ካፍ በኮትዲቯር የሚዘጋጀውን የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማራዘሙን አስታወቀ
ውድድሩ የተራዘመው በኮትዳቯር "በሚኖረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ” ምክንያት ነው ተብሏል
የካፍ ፕሬዝዳነቱ ፓትሪስ ሞሴፔ ኮትዲቯር ውድድሩን ለማዘጋጀት ከወዲሁ ላደረገችው ዝግጅት አድንቋል
በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ከሰኔ እስከ ሃምሌ 2023 በኮትዲቯር ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲራዘም መወሰኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታወቀ፡፡
ውድድሩ እንዲራዘም የተደረገው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጉዳዩ ላይ ለስብሰባ ከተቀመጠ በኋላ ነው፡፡
በዚህም መሰረት 34ኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር በሚቀጥለው ዓመት በኮትዲቯር ውስጥ እንዲካሄድ መርሃ-ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም፣ ወቅቱ በሀገሪቱ ከባድ ዝናብ የሚጥልበት በመሆኑ ነው ለቀጣይ ዓመት የተሸጋገረው።
ደቡብ አፍሪካዊው የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር እየተካሄደባት ካለችው ሞሮኮ ራባት ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት "በሚኖረው የአየር ሁኔታ ምክንያት ምንም ማድረግ አንደፍርም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የዓለም ዋንጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ በሚቀጥለው ዓመት ህዳርና ታህሳስ ወር ላይ የሚካሄድ በመሆኑ፣ የአፍሪካ ዋንጫን ወደፊት ከማምጣት ይልቅ ወደ ቀጣይ ዓመት ማሸጋገሩ የግድ ሆኗልም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
በዚህም ምክንያት “የአፍሪካ ዋንጫ በዚህ ዓመት ካሜሩን ውስጥ እንደተካሄደው ሁሉ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በጥር እና የካቲት ይከናወናል” ሲሉም አክለዋል።
ውድድሩ ወደ ሰኔ እና ሃምሌ ማዘዋወሩ የአውሮፓ ክለቦች በውድድር ላይ ሳሉ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ተጫዋቾችን እንዲለቁ በመጠየቅ የሚነሳውን ውዝግብ ለማስቀረት ያለመ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳነት አክለው "በአውሮፓ ክለቦች ምክንያት ጥር ለውድድሩ አመቺ ወቅት አይደለም፣ ነገር ግን ለአሁን ያለን ብቸኛው አመራጭ እሱ ነው”ም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ የካፍ ፕሬዝዳንቱ ፓትሪስ ሞሴፔ ኮትዲቯር ውድድሩን ለማዘጋጀት ከወዲሁ ላደረገችው ዝግጅት አድንቋል።
ሞሴፔ "በኮትዲቯር ለውድድሩ ዝግጁነት በተዘረጋው መሰረተ ልማት ደስተኛ እና ተደንቄያለሁ እናም በጣም ጥሩ ውድድር እንደሚያዘጋጁ እርግጠኛ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።
በቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ የአመራር ዘመን የአህጉሪቱ መለያ የሆነውን የእግር ኳስ ውድድር ማካሄጃ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት የማሸጋገሩ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ተቀባይነት ሳያገኝ የቆየ ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል።