የካሜሮን ተገንጣይ ታጣቂዎች ሀገሪቱ በምታዘጋጀው “የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ስጋት ደቅነዋል” ተባለ
የምድብ-ኤፍ (F) ሀገራትን የሚያስተናግደው “የሊምቤ ኦምኒስፖርት ስታዲየም የተገንጣዮቹ ዒላማ እንዳይሆን” ተሰግቷል
የካሜሮን ባላስልጣናት “ከጥቂት ወራት በፊት ቻንን እንዳስተናገድን ሁሉ የአፍሪካ ዋንጫም በስኬት ይጠናቀቃል” እያሉ ነው
የካሜሮን ተገንጣይ ታጣቂዎች ሀገሪቱ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ስጋት ሳይደቅኑ እንዳልቀረ በመገለጽ ላይ ነው፡፡
በዚህም የሀገሪቱ መንግስት ጥር 9/2022 የሚጀመረውን የአፍሪካ ዋንጫ ምንም አይነት እክል እንዳይገጥመው በሚል ፤ ግጭት በሚስተዋልበትና በሀገሪቱ ደቡብ ምዕራብ ክልል በምትገኘው ሊምቤ ከተማ አከባቢ በርካታ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች ማሰማራቱ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካሜሩን ውድድሩን በስድስት ከተሞች የምታስተናግድ ሲሆን፤ በ2017 ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት በሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች እየተናጠች የምትገኘው ሊምቤ ከተማ አንዷ ናት፡፡
አምባዞንያ የምትባል ተገንጣይ ግዛት የመመስረትን ዓላመ አንግበው የካሜሮን መንግስትን ለመጋፈጥ ነፍጥ እንዳነገቡ የሚነግርላቸው ተገንጣይ ታጣቂዎቹ፤ አስካሁን በሰነዘሩት ጥቃት ቢያንስ 3 ሺህ ሰዎችን ገድሏል እንዲሁም ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አከባብያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል።
ተገንጣዮች በዚህ ዓመት ዘመናዊ ፈንጂዎች መጠቀማቸው ሁኔታው ይበልጥ መባባሱንም ነው የተገለጸው፡፡
የሀገር ውስጥ ጋዜጠኛ ሆኖሬ ኩማ "የእኔ ፍራቻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሊምቤ አከባቢ የሚታየው የቦምብ ፍንዳታ ክስተት በዚህ የአፍሪካ ዋናጫ ወቅት የተለመደ ክስተት ሊሆን ይችላል" የሚል ስጋቱን አስቀምጧል፡፡
የሊምቤ ኦምኒስፖርት ስታዲየም ከምድብ F ቱኒዚያ፣ማሊ፣ ሞሪታንያ እና ጋምቢያን ያቀፈ ጨዋታዎችን እንደሚያስተናግድና የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በጥር 12 በቱኒዚያ እና በማሊ መካከል እንደሚደረግም ነው የተገለጸው።
ከደህንነት ጉዳዩ በተጨማሪ የስታዲየሞች ዝግጁነት እና የኦሚክሮን ኮቪድ-19 መዛመት ለአፍሪካ ዋንጫው ሌላ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆነዋልም ነው የተባለው፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሰል የደህንነት ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገለጽ ላይ ቢሆኑም የካሜሮን ባለስልጣናት በምድብ ኤፍ ላይ ምንም አይነት መስተጓጎል እንደማይኖር ከወዲሁ ቃል ገብቷል።