ከስምንት ሴቶች አንዷ ከ18 አመቷ በፊት ተደፍራለች ወይም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባታል - ዩኒሴፍ
የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከ370 ሚሊየን በላይ ሴቶች ከ18 አመታቸው በፊት ተደፍረዋል አልያም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል
ሪፖርቱ ከ11 ወንዶቹ አንዱ የአስገድዶ መደፈርና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ መሆኑን አመላክቷል
በአለማችን በአሁኑ ወቅት ከ370 ሚሊየን በላይ ሴቶች (ከስምንቱ አንዱ) ከ18 አመታቸው በፊት ተደፍረዋል አልያም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል አለ ዩኒሴፍ።
የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባወጣው አዲስ ሪፖርት “ከንክኪ ውጪ የሆኑ” በኦንላይን እና በቃላት የሚፈጸሙ ጾታዊ ትንኮሳዎች ከተቆጠሩ አሃዙ ወደ 650 ሚሊየን ከፍ እንደሚል አመላክቷል።
ዩኒሴፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በችግሩ ዙሪያ አደረግኩት ባለው አለማቀፍ የዳሰሳ ጥናት ወንዶችም የአስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ነው የጠቆመው።
ከ240 እስከ 310 ሚሊየን የሚደርሱ ወንዶች በልጅነታቸው ተደፍረዋል አልያም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ነው ያለው የዩኒሴፍ ሪፖርት።
ከ11 እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ከሆኑ ወንዶች ውስጥ አንዱ ለአስገድዶ መደፈር ወይንም ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ ነው ያለው ድርጅቱ፥ ግኝቱ የችግሩን አሳሳቢነት በጉልህ ማመላከቱን ገልጿል።
ከስሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የጾታዊ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ውስጥ በቀዳሚነት ተቀምጠዋል፤ 79 ሚሊየን ሴቶችና ልጃገረዶች (22 በመቶ) የጥቃቱ ተጋላጭ ናቸው።
በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ደግሞ በ75 ሚሊየን የጥቃቱ ሰለባ ሴቶች ተከታዩን ደረጃ ይይዛሉ።
በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ 45 ሚሊየን፤ በላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን 29 ሚሊየን እንዲሁም በሰሜን አፍሪካና ምዕራብ እስያ 29 ሚሊየን ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት መጋለጣቸውንም ሪፖርቱ አመላክቷል።
የሰላም ችግር ባለባቸው፣ የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በተሰማሩባቸውና በርካታ ስደተኞች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለጥቃቱ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው ይላል ዩኒሴፍ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል በህጻናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት “ህሊናን የሚያጎድፍ ተግባር ነው፤ ተጎጂዎች ላይ ዘላቂና ጥልቅ ድባቴ ያስከትላል” ብለዋል።
የሚደፈሩት ወይም ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው በአብዛኛው በሚያውቁትና በሚያምኑት ሰው መሆኑም የሚፈጥረው እምነት የማጣት ቀውስ ቀላል አይደለም ነው ያሉት።
አብዛኛው የጾታዊ ጥቃት የሚፈጸመው እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 አመት ባሉ ታዳጊዎች ላይ መሆኑንና ተጠቂዎቹ በጾታዊ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች እና የአዕምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ መሆኑንም አብራርቷል።
ታዳጊዎቹ በተለይም ወንዶች የሚደርስባቸውን ጾታዊ ጥቃት ለመናገር አይደፍሩም የሚለው የዩኒሴፍ ሪፖርት፥ ሀገራት ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሚሰበስቡበትን መንገድ እንዲያዘምኑ ጥሪ አቅርቧል።
ዩኒሴፍ የዳሰሳ ጥናቱን ያደረገው 120 ሀገራት ከ2010 እስከ 2022 ያደረጓቸውን ጥናቶች መሰረት በማድረግ መሆኑን ይፋ አድርጓል።