በ90 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የተከሰሰው ደቡብ አፍሪካዊ 42 የእድሜ ልክ እስራቶች ተፈረዱበት
ተከሳሹ ከፖሊስ ለማምለጥ ጥረት ሲያርግ በተተኮሰበት ጥይት አንድ እግሩን አጥቷል
ከ2012 – 2021 ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ተከሳሽ የ9 ዓመት ህጻናትን ጨምሮ 90 ሴቶችን አስገድዶ መድፈሩ ተረጋግጧል
ንኮሲናቲ ፋካቲ የተባለው የ40 አመት ደቡብ አፍሪካዊ ለ9 አመታት በፈጸማቸው ተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች 42 የእድሜ ልክ እስራቶች ተፈርዶበታል።
90 የአስገድዶ መድፈር ክሶች የቀረቡበት ተከሳሾቹ እድሜያቸው 9 አመት የሚደርሱ ህጻናትን ጨምሮ በተለያዩ እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶችን አስገድዶ መድፈሩ ተረጋግጧል።
ግለሰቡ ህጻናት ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ሲፈጽም እንዲመለከቱት ያስገድድ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ህጻናት ወንዶች ሴት ጓደኞቻቸውን አስገድደው እንዲደፍሩ ያስደርግ እንደነበር በክስ መዝገቡ ላይ ተገልጿል።
እኩርሁሌኒ በተባለው ከጆሀንስበርግ በምስራቅ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ ከተማ ወንጀሉ መፈጸሙን ለጆሀንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስረዳው አቃቤ ህግ ግለሰቡ የአስገድዶ መድፈርን ጨምሮ እገታ ፣ ስርቆት እና በድብደባ ክሶች አቅርቦበታል።
ከ9 አመት-44 አመት እድሜ ያላቸውን ሴቶች የሚደፍረው ግለሰብ አብዘሀኛዎቹ ተጠቂዎች በታዳጊ እድሜ ላይ የሚገኙ ሴት ተማሪዎች መሆናቸው ሲነገር ህጻናቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ወይም ሲመለሱ አፍኖ በማገት ድርጊቱን እንደሚፈጽም ታውቋል፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ሰራተኛ እንደሆነ በማስመሰል በሰዎች መኖርያ ቤቶች ውስጥ በመሄድ ወንጀሉን ለ9 አመታት ወንጀል መፈጸሙ ነው የተነገረው።
በ2021 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ተከሳሹ ከፖሊስ ለማምለጥ ጥረት ሲያርግ በተተኮሰበት ጥይት አንድ እግሩን አጥቷል።
ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ "ፍርድ ቤቶቻችን እንደዚህ አይነት ወንጀል በተለይም ወጣት፣ ንፁህ፣ እና እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ተጋላጭ ሴት ልጆች ላይ ሲፈጸም አስተማሪ ከፍተኛ የቅጣት ውሳኔ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን" ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተከሳሹ ምንም አይነት የጸጸት ስሜት የማይስተዋለበት እና የማይሻሻል ሰው ነው ያሉት ዳኛው 42 የእድሜ ልክ እስራቶችን እንዲቀጣ ወስነዋል፡፡
በነፍስ ግድያ በአስገድዶ መድፈር እና በሌሎች አስቃቂ ወንጀሎች መስፋፋት ችግር ውስጥ የምትገኝው ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የወንጀል ምጣኔ ከሚገኝባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡
ባለፈው አመት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ በሶስት ወራት ብቻ 9300 የአስገድዶ መድፈሮች ሲፈጸሙ ይህም ወንጀሉ በ0.6 በመቶ መጨመሩን እንደሚያመላክት የፖሊስ መረጃ ያሳያል፡፡