በደቡብ አፍሪካው ሁከት ምክንያት 40ሺ የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን መንግስት አስታወቀ
ደቡብ አፍሪካ በተፈጠሩ ሁከቶች ምክንያት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ንብረት ወድሞብኛል አለች
በሁከት እስካሁን የ215 ሰዎች ህይወት ማለፉን የደቡብ አፍሪካ መንግስት ገልጿል
በደቡብ አፍሪካ ባለፉት 15 ቀናት በተፈጠረው ሁከት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ንብረት እንደወደመ መንግስት አስታውቋል።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰርን ምክንያት በማድረግ በተቀሰቀሰ ግጭት ሀገሪቱ ሁከት እና ብጥብጥን አስተናግደዋል።የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤትን ዋቢ አድርጎ ሲጂቲኤን እንደዘገበው በደቡብ አፍሪካ በተፈጠረው ሁከት 40 ሺህ የንግድ ተቋማት የዘረፋ፤ቃጠሎ እና የመውደም አደጋ አስተናግደዋል።
በተለይም በኩዋዙሉ ናታል ግዛት ያሉ የንግድ መደብሮች፤የሽያጭ ሱቆች እና ሌሎች መሰል ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ክስተቱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተጎዳው የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚን ወደ ባሰ ጉዳት ይከተዋል የሚለኩ አስተያየቶችም በመሰጠት ላይ ናቸው።
ጉዳቱ በገንዘብ ሲለካም 50 ቢሊዮን ራንድ ወይም 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት እንዲወድም ምክንያት መሆኑን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
በዚህ አደጋ ካሉ ከ200 በላይ ሱቆች ውስጥ 100ዎቹ ሙሉ በሙሉ የተቃጠሉ ወይም የተዘረፉ ሲሆን ቢያንስ 1 ሺህ 400 የባንክ ኤቲኤሞች ሲወድሙ 300 ባንኮች እና የፖስታ ማዕከላት መቃጠላቸው ተገልጿል።
ሁከቱ ያደረሰው ጉዳት እስካሁን በኩዋዙሉ ናታል እና ደቡባዊ የአገሪቱ ከፍል የተጣራ ሲሆን በጓቲንግ ግዛት ደግሞ የጉዳቱ መጠን ገና በመጠናት ላይ ነው ተብሏል።
ኩዋዙሉ ናታል እና ጉዋቲንግ ግዛቶች የደቡብ አፍሪካ ዋነኛ የንግድ ማዕከላት ሲሆኑ ከግማሽ በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት መጠን ድርሻ ያላቸው ሲሆን በዚህ ሁከት ክፉኛ ከተጎዱ ግዛቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ፕሬዘዳንት ራማፖሳ ሁከቱን ለመቆጣጠር መንግስት አስቀድሞ ዝግጁ እንዳልነበር ገልጸው የጸጥታ ሀይሉ ጉዳቶች ቶሎ ለመቆጣጠር እንዳልቻለ አምነዋል።
በዚህ አደጋ ምክንያት የ215 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ባለፉት 24 ሰዓታት ምንም አይነት የሰው ህይወት እንዳላለፈ ተገልጿል።በሁከቱ የተጠረጠሩ 2 ሺህ 500 ሰዎች በፖሊስ የተያዙ ሲሆን 200ዎቹ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ተገልጿል።