በአመጹ የ72 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃብ ዙማ መታሰርን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አመጽ በሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።
6ኛ ቀኑን በያዘው አመጽ የ72 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ የተለያዩ መጋዘኖችና ግምጃ ቤቶች እንዲዘረፉም ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።
የዘረፋ ሰለባ ከሆኑት ውስጥም ፋርማሲዎች እንደሚገኙበት የደቡብ አፍሪካ የፋማሲዎች ካውንስል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በአመጹም እስካሁን ከ90 በላይ የመድሃኒት መደብሮች መውደማቸውን እና መዘረፋቸውን የሀገሪቱ ካውንስል መግለጹን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ከተዘረፉ መድሃኒቶች ውስጥ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶች መዘረፋቸውን የደቡብ አፍሪካ የፋማሲዎች ካውንስል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በተጨማሪም ያለ ሀኪም ምክር ሊወሰዱ የማይገቡ እና ለሰዎች በቀጠሮ ብቻ የሚሰጡ መድሃቶችም ተሰርቀዋል ያለው ካውንስሉ፤ መድሃቶቹን ያለ ሀኪም ትእዛዝ መውሰድ በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ገልጿል።
ሰዎች የሰረቋቸውን መድሃቶች ለራሳቸውም ይሁን ለሌላ ሰው ከመስጠት እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ካውንስሉ፤ በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ ፋርማሲ እንዲሰጡም ጠይቋል።
በደቡብ አፍሪካው አመጽ ከመድሃኒቶች በተጨማሪም ፤ አንድ ማህበረሰብ ጣቢያን ጨምሮ ምግቦች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ አረቄዎች እና አልባሳት ከመደብሮች መሰረቃቸውም ታውቋል።
የኤ.ቲ.ኤም ማሽን ለማቃጠል ሁከት ፈጣሪዎች በወረወሩት ቦምብ ምክንያት በተፈጠረ ፍንዳታ የሰዎች ህይወት ማለፉም ታውቋል።
በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰርን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አመጽ እስካሁን የ72 ሰዎች ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በችሎት መድፈር 15 የእስር ወራት የተላለፈባቸው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ እጄን ለፖሊስ አልሰጥም ሲሉ ከቆዩ በኋላ ከአንድ ሳምንት በፊት እጅ መስጠታቸው ይታወሳል።
የ79 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ እስር ቤት መግባታቸው እንዲዘገይ ያቀረቡት ማመልከቻ በፒተርማርቲዝበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ዙማ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ሆኗል።
በዚህም ምክንያት ዙማ ካላፈው ሐሙስ አንስቶ የ15 ወራት እስራታቸው ጀምረዋል።