በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ንብረታቸው እየተዘረፈባቸው መሆኑን ተናገሩ
እስካሁን ድረስ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያዊያን አሉ የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል
በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ንብረታቸው እየተዘረፈባቸው መሆኑን ተናገሩ።
በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰርን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አመጽ እስካሁን የ72 ሰዎች ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አል ዐይን አማርኛ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያሉበትን ሁኔታ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎችን ጠይቋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የጆሀንስበረግ እና የፕሪቶሪያ ከተሞች ነዋሪዎች እንዳሉት በደቡብ አፍሪካ ከተሞች ሁከት ከተከሰተ በኋላ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑ ላይ ነው።
እስካሁን ባለው ሁከት ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን እንዳልሰሙ ነግረውናል።
ይሁን እንጂ ንብረቶቻቸው የተዘረፈባቸው እና በእሳት የወደመባቸው ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በከተሞቹ ንብረት ዘረፋና ወከባ መኖሩን የተናገሩት እነዚህ ነዋሪዎች ሁከቱ ዛሬ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ፖሊስ ዘረፋውን እና እሳት አደጋውን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም አለመቻሉ ሁከቱ አሁንም ሊቀጥል የሚችል ስጋት እንዳላቸው ነግረውናል።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው አመጽና ሁከት፤ በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ሞት ባይከሰትም መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደር ሽፈራው፤ ጉዳት ያጋጠማቸው የኢትዮጵያ ዜጎች እየታከሙ መሆኑን ያነሱም ሲሆን ኤምባሲው ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን፤ እየተካሄደ ያለውን የንብረት ዘረፋና ቃጠሎ በተመለከተ ከደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፤ ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንም ነው ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡
አመጽ እየተደረገባቸው ያሉት የሀውቴን ግዛት በጆሃንስበርግና በፕሪቶሪያ ከተሞች መካከልና አካባቢ ያለ ሲሆን ክዋዙሉ ናታል ደግሞ በደርባን አካባቢ የሚገኙ ግዛቶች ናቸው፡፡
አምባሳደሩ እንዳሉት የተዘረፉና ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ዜጎች እንዲያገግሙ ለማድረግ ትክክለኛ መረጃ እየተሰባሰበ ይገኛል፡፡
በችሎት መድፈር 15 የእስር ወራት የተላለፈባቸው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ እጄን ለፖሊስ አልሰጥም ሲሉ ከቆዩ በኋላ ከአንድ ሳምንት በፊት እጅ መስጠታቸው ይታወሳል።
የ79 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ እስር ቤት መግባታቸው እንዲዘገይ ያቀረቡት ማመልከቻ በፒተርማርቲዝበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ዙማ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ሆኗል።
በዚህም ምክንያት ዙማ ካላፈው ሐሙስ አንስቶ የ15 ወራት እስራታቸው ጀምረዋል።