የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አዛዡ ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎም በዚህ ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ
በ42ኛ የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአባል ሀገራቱ መሪዎች ኡጋንዳ እየገቡ ነው።
በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሚመክረው ጉባኤ ለመሳተፍ የኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንቶች ካምፓላ መግባታቸውን የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከኢጋድ ጋር ግንኙነቴን አቋርጫለሁ ያለችው ሱዳን ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልቡርሃን በዚህ ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
ካርቱም በጉባኤው ላይ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ ጅነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቴ) መጋበዛቸው ሉአላዊነቴን ይጥሳል በሚል ነው ከክፍለ ቀጠናዊው ድርጅት ጋር ግንኙነቷን ማቋረጧን ያስታወቀችው።
ሄሜቲ በኢጋድ 42ኛ ጉባኤ ለመሳተፍ ካምፓላ መግባታቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷ የሻከረው ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ መሳተፏን አላረጋገጠችም።
በካምፓላው የኢጋድ ጉባኤ የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎችን ፊት ለፊት ለማገናኘት የተያዘው ውጥን ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዘጠኝ ወራት በፊት የተቀሰቀሰውና ከ12 ሺህ በላይ ሱዳናውያንን ህይወት የቀጠፈው የሁለቱ ጀነራሎች ፍልሚያ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ አስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊ አድርጓል።
ተፋላሚዎቹ በየፊናቸው የጎረቤት ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ውጭ እስካሁን ለጦርነቱ መቋጫ የሚሆንና የሚያስማማ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ሲጥሩ አልታየም።
በኡጋንዳ ዛሬ በሚጀመረው ጉባኤ ለመሳተፍ ካምፓላ የገቡት ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ በጦርነቱ ድል እየቀናቸው ነው የተባለ ሲሆን፥ በስድስት ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶችም የሉአላዊ ምክርቤቱን ፕሬዝዳንት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት ሀገራት ጉብኝት ያደረጉት ጀነራል ዳጋሎ ከጦር ሜዳው ባሻገር በውጭ ግንኙነቱና ዲፕሎማሲውም መሪነቱን ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት ውጤት እያሳየ መምጣቱን ተንታኞች ይገልጻሉ።