የሱዳን መንግስት ከኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋረጠ
ኢጋድ ነገ በኡጋንዳ በሚያደርገው ጉባኤ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን አዛዥ መጋበዙ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ይዳፈራል በሚል ነው ግንኙነቱን ያቋረጠው
ኢጋድ የሱዳን መንግስት ላነሳው ቅሬታ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም
የሱዳን መንግስት ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ባለስልጣል (ኢጋድ) ጋር ያለውን ግንኙነት አቋረጠ።
የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎችን ፊት ለፊት ለማደራደር ጥረት እያደረገ የሚገኘው ኢጋድ በካምፓላው ጉባኤ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን አዛዥ መጋበዙ ነው የሱዳን መንግስትን ያስቆጣው።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የሄሜቲ በኢጋድ ጉባኤ እንዲሳተፉ መጋበዝ የሱዳንን ሉአላዊነት ይዳፈራል ብሏል።
መግለጫው ኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባውን ሲጠራም ሆነ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን መሪ ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ሲጋብዝ አስቀድሞ የሱዳን መንግስትን አላማከረም ይላል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ ግብዣ የኢጋድን ቻርተር ብሎም የአለማቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶችን ህግጋት የተቃረነ መሆኑን በመጥቀስም በካምፓላው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ እንደማይሳተፍ አስታውቋል።
የሱዳን መንግስት “በኢጋድ ታሪክ አደገኛ አካሄድ ነው” ያለውን የሄሜቲ ግብዣ ለወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ጂቡቲ በደብዳቤ ማሳወቁንም ጠቅሷል።
ኢጋድ የሱዳን መንግስት ላነሳው ቅሬታና ከድርጅቱ ጋር ግንኙነቴን አቋርጫለሁ በሚል ላወጣው መግለጫ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የሱዳን ጦር መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ጀነራል ዳጋሎን ተቀብለው ማስተናገዳቸውን መቃወማቸው የሚታወስ ነው።
ከዘጠኝ ወራት በፊት የተቀሰቀሰውና ከ12 ሺህ በላይ ሱዳናውያንን ህይወት የቀጠፈው የሁለቱ ጀነራሎች ፍልሚያ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ አስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊ አድርጓል።
ተፋላሚዎቹ ጀነራሎች በየፊናቸው የጎረቤት ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ውጭ እስካሁን ፊት ለፊት ተገናኝተው ለጦርነቱ መቋጫ መፍትሄን ለማበጀት ሲጥሩ እምብዛም አልታየም።