ሶማሊያ ወደ ሀርጌሳ እየበረረ የነበረ እቃ ጫኝ አውሮፕላን እንዳያርፍ መከልከሏን አስታወቀች
የተሟላ የበረራ መረጃ የሌለው አውሮፕላን በግዛቷ እንዳያርፍ መከልከሏን እንደምትቀጥልም ገልጻለች
ሶማሊያ በ24 ሰዓታት ውስጥ የኢትዮጵያን ጨምሮ ሁለት አውሮፕላኖች እንዳያርፉ እገዳ ጥላለች
ሶማሊያ ወደ ሀርጌሳ እየበረረ የነበረ እቃ ጫኝ አውሮፕላን እንዳያርፍ መከልከሏን አስታወቀች።
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ንብረትነቱ የታይላንድ የሆነ P4-JAG የተሰኘ የእቃ ጫኝ አውሮፕላን ወደ ሀርጌሳ በመብረር ላይ ነበር ብላል።
ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ ይህ የእቃ ጫኝ አውሮፕላን ወደ ሀርጌሳ እንዳይበር እና እንዳያርፍ መከልከላንም አስታውቃለች።
ከሻርጃህ እንደተነሳ የተገለጸው ይህ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በታይላንድ የተመዘገበ ነው ከመባሉ ውጪ ባለቤቱ በመግለጫው ላይ አልተጠቀሰም።
በረራውን እያደረገ የነበረው አውሮፕላን ተጨማሪ መረጃ ሲጠየቅ መስጠት እንዳልቻለም ተገልጿል።
የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተሟላ የበረራ መረጃ ያላቀረበ አውሮፕላን እንዲበር እና እንዲያርፍ ፈቃድ መከልከሉን እቀጥላለሁም ብላል።
ባለስልጣኑ በትናንትናው ዕለት ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የበረራ ቁጥሩ ET8372 የተሰኘ አውሮፕላን ወደ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በረራ በማድረግ ላይ እያለ እንዲመለስ አድርጌያለሁ ማለቱ ይታወሳል።
እንዲመለስ የተደረገው አውሮፕላን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ይዞ እንደነበር ብሉምበርግ በጉዳዩ ዙሪያ በተጨማሪነት ባወጣው ዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ "በተደረገው ተጨማሪ ውይይት ተከልክሎ የነበረው አውሮፕላን ትናንት አመሻሽ ወደ ሀርጌሳ እንዲበር ተደርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።
ከሶስት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ተነስቷል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት በዚሁ መግባቢያ ስምምነት ዙሪያ እና በሱዳን ሰላም ጉዳይ ለመምከር አስቸኳይ ጉባኤውን በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ እያደረገ ይገኛል።