እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 61 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
አሁን ስደተኞችን ባስጠለሉ በጋዛ ከተማ እና በጃባሊያ በሚገኙ ሁለት የቀድሞ ትምህርት ቤቶች ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው
የእስራኤል ጦር ግን የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በቦታው ሰፍረው በነበሩ የሀማስ ታጣቂዎች ላይ ነው ብሏል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 61 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
የእስራኤል የአየር ኃይል በመላው ጋዛ ውስጥ በ48 ሰአታት ውስጥ በፈጸማቸው ጥቃቶች 61 ሰዎች መገደላቸውን ሮይተርስ የጤና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት 11 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና የእስራኤል እና የውጭ ታጋቾችን ለማስለቀቆ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አልተሳኩም።
የፍልስጤም የጤና ባለሙያዎች እንደገለጹት አሁን ስደተኞችን ባስጠለሉ በጋዛ ከተማ እና በጃባሊያ በሚገኙ ሁለት የቀድሞ ትምህርት ቤቶች ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው።
የእስራኤል ጦር ግን የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በቦታው ሰፍረው በነበሩ የሀማስ ታጣቂዎች ላይ ነው ብሏል።
የሀማስ ታጣቂ ክንፍ፣ እስላማዊ ጂሀድ እና ፋታህ ቡድን በመላው ጋዛ የእስራኤልን ጦር በጸረ-ታንክ፣በሞርታር ቦምቦች እና በአንድ አንድ ቦታዎች ደግሞ ታንኮችን ለማውደም ቦምብ እያጠመዱ መሆናቸዉን ተናግረዋል።
ሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች ኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካን ጨምሮ አዳረዳሪዎች ተኩስ እንዲያቆሙ የተደረገው ጥረት እንዳይሳካ በማድረግ አንዳቸው ሌላኛቸውን ይወቅሳሉ።
አሜሪካ አዲስ የስምምነት ሀሳብ ለማቅረብ እየተዘጋጀች ቢሆንም በሁለቱ መካከል ልዩነቱ ሰፊ ሆኖ በመቀጠሉ የመሳካት እድሉ አነስተኛ ነው ተብሏል። የአሜሪካ ዋና አደራዳሪ የሆኑት የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ለንደን በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት የእቅዱ ዝርዝር ይዘት በቀጣይ ቀናት ይፋ ይደረጋል።
በቴል አቪቭ እና በሌሎች ከተሞች የሚኖሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሀማስ እጅ የሚገኙት 101 ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት ታግተው ከሚገኙት ውስጥ ስድስቱ ተገድለው በመገኘታቸው የተናደዱ እና ያዘኑ ናቸው ወደ አደባባይ የወጡት።
እስራኤል አነዚህ ስድስት ታጋቾች በጋዛ በሚገኝ ቱቦ ውስጥ ጭንቅላታቸውን ተመትተው መገደላቸውን አስከሬናቸው በወታደሮች ተቆፍሮ ከተገኘ በኋላ ብዙም ሳትቆይ ይፋ አድርጋ ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ያደረገው ሀማስ እና እስራኤል ስምምነት ላይ የመድረስ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በእስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት እስካሁን ከ40ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።