ሃማስ ተኩስ ካልቆመ ሁሉም ታጋቾች ወደ እስራኤል የሚመለሱት “በአስከሬን ሳጥን” ነው ሲል ዛተ
የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ታጋቾቹን ለሚጠብቁ ሃይሎች አዲስ ትዕዛዝ ማስተላለፉንም አስታውቋል
በእስራኤል የተለያዩ ከተሞች ኔታንያሁ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ እስራኤል ወታደራዊ ጫናዋን ከቀጠለች በጋዛ የሚገኙ ታጋቾች ወደ እስራኤል የሚመለሱት “በአስከሬን ሳጥን” ነው ሲል አስጠነቀቀ።
“ኔታንያሁ ታጋቾቹን ለማስለቀቀ ከድርድር ይልቅ የሃይል እርምጃን መርጧል፤ ስለዚህ ታጋቾቹ ወደ እስራኤል በህይወት ሊመለሱ አይችሉም” ብለዋል የአልቃሳም ብርጌድ ቃል አቀባይ አቡ ኦዴይባ።
ታጋቾቹን ለሚጠብቁ የቡድኑ ተዋጊዎች አዲስ ትዕዛዝ መተላለፉንም ነው የተናገሩት።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በራፋህ ቱቦ ውስጥ ተገኝተዋል የተባሉትን ታጋቾች ህይወት መታደግ ባለመቻሉ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ኔታንያሁ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ታጋቾቹን ገድሏል ያሉት ሃማስ “ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ ዝተዋል።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ኢዛት አል ሪሼቅ ግን ስድስቱ ታጋቾች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን መናገራቸውን ስካይኒውስ ዘግቧል።
ሃማስ ለታጋቾቹ ግድያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗል ያለውን የኔታንያሁ አስተዳደር ተጠያቂ አድርጓል።
የታጋቾቹ ግድያ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ በትናንትናው እለትም ሳይበርድ በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ውለዋል።
በሰልፎቹ “ኔታንያሁ የታጋቾቹ ህይወት ግድ አልሰጣቸውም፤ ስልጣን ለቀው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረስ” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከህዝቡ እና ከአጣማሪዎቻቸው ጭምር ተቃውሞው ቢበረታማቸውም በጋዛ “ሃማስን ካልደመሰስን ጦርነቱ አይቆምም” በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል።
በትናንቱ መግለጫቸውም የእስራኤል ጦር የጋዛውን የፊላደልፊያ መተላለፊያ መቆጣጠሩ የግድ ነው ብለዋል።
መተላለፊያው እስራኤልና ሃማስ በሚያደርጉት የተኩስ አቁም ድርድር ከሚነሱ ወሳኝ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው።