የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች ከአራት አመታት እስር በኋላ ተለቀቁ
ፓርቲው ሁለት የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ፣አንድ የብሔራዊ ምክር ቤት አባሉ እና አራት ኦፊሰሮቹ ከእስር ተፈትተዋል ብሏል
ፓርቲው "እነዚህ ግለሰቦች የታሰሩት ህጋዊ የፖለቲካ መብታቸውን እና በኦነግ ውስጥ ድርጅታዊ ስራ በመስራታቸው መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው"ብሏል
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ከአራት አመታት እስር በኋላ በዋስ መለቀቃቸውን ፓርቲው በትናንትናው እለታ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ፓርቲው እንደገለጸው አመራሮቹ እና አባላቶቹ ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ በእስር ቆይተዋል።
ፓርቲው ሁለት የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ፣አንድ የብሔራዊ ምክር ቤት አባሉ እና አራት ኦፊሰሮቹ ከእስር ተፈትተዋል ብሏል።
ከተለቀቁት አባላት መካከል የግንባሩ የስራ አስፈጻሚ አባላት አብዲ ረጋሳ እና ሚካኤል ቦራን፣ የግንባሩ ብሔራዊ ምክርቤት አባል ከኔሳ አያና፣ የግንባሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ኦፊሰሮች ለሚ ቤኛ፣ ዶክተር ገዳ ኦልጅራ፣ ገዳ ጋቢሳ እና ዳዊት አብደታ ይገኙበታል ብሏል መግለጫው።
የአመራሮቹ እና አባላቱ ከእስር መፈታት እንዳስደሰተው የገለጸው ኦነግ "እነዚህ ግለሰቦች የታሰሩት ህጋዊ የፖለቲካ መብታቸውን እና በኦነግ ውስጥ ድርጅታዊ ስራ በመስራታቸው መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው"ብሏል።
ፓርቲው ግለሰቦቹ በፍርድ ቤት ለበርካታ ጊዜ ነጻ ተብለው መለቀቃቸውንም አስታውሷል።
ፓርቲው መሪዎቹ እና አባላቱ እንዲለቀቁ ግፋት ሲያደርጉ ነበር ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን(ኢሰመኮ) አመስግኗል።
ኢሰመኮን እና አለም አቀፍ የመብት ተቋማት የኦነግ አመራሮች እንዲፈቱ የሚጠይቁ መግለጫዎች በተለያየ ጊዜ ማውጣታቸው ይታወሳል።