በቅባታማ ምግቦች 5 ቢሊየን ህዝብ ለልብ ህመም ተጋላጭ ሆኗል- የአለም ጤና ድርጅት
ድርጅቱ ከ2018 ጀምሮ ሀገራት በኢንዱስትሪ ከሚያመርቷቸው ምግቦች የስብ አሲዶችን እንዲያስወግዱ ጠይቆ ነበር
ግብጽ፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ ኮሪያ በርካታ ዜጎቻቸው ለልብ ህመም እየተጋለጡባቸው ከሚገኙ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
5 ቢሊየን ህዝብ በስብ እና ቅባታማ ምግቦች ምክንያት ለከፍተኛ የልብ ህመም ተጋላጭ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት ገለጸ።
ድርጅቱ ሀገራት ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን ለማስተካከል የሚወስዷቸው እርምጃዎችን እንዲያሻሽሉ አሳስቧል።
በተለት በኢንዱስትሪ ከሚያመርቷቸው ምግቦች የስብ አሲዶችን እንዲያስወግዱ የጠየቀው የአለም ጤና ድርጅት ሀገራት እየሰጡት ያለው ምላሽ በጣም ዝቅተኛ ነው ብሏል።
ድርጅቱ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በፋብሪካዎች የሚመረቱ ምግቦች ከጎጂ ኮሊስትሮል የተላቀቁ እንዲሆኑ ቢወትውትም እስካሁን ተገቢውን ምላሽ የሰጡት 43 ሀገራት ብቻ ናቸው።
በዚህም 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ሰዎችን ከከፍተኛ የልብ ህመም ተጋላጭነት መታደግ ቢቻልም፥ ከ5 ቢሊየን በላይ ህዝብን የያዙ ሀገራት ፈጣን ምላሽ ካልሰጡ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ስለመሆኑም ነው የአለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው።
ግብጽ፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ ኮሪያ በስባማ ምግቦች ምክንያት በርካታ ዜጎቻቸው ለልብ ህመም እየተጋለጡባቸው ከሚገኙ ሀገራት መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።
“ታራንስ ፋት” በተጠበሱ እና በማሽን በተዘጋጁ ምግቦች እና ዘይቶች ውስጥ የሚገኝ ለጤና አደገኛ የሆነ መጥፎ ቅባት ነው።
የደም ቧንቧዎችን በመዝጋትና የደም ዝውውርን በመግታት ለልብ እና ሌሎች ህመሞች ተጋላጭ ያደርጋል።
ጤናማ ያልሆኑ ቅባታማ ንጥረነገሮችን የያዙት ምግቦች ከመጠን ያለፈ ክብደትን እንደሚያስከትሉም ነው የጤና ባለሙያዎች የሚገልጹት።
ምግብ አምራች ግን ለረጅም ጊዜ ሳበላሹ ስለሚቆዩና ርካሽ ስለሆኑ ይመርጧቸዋል።
የአለም ጤና ድርጅት ግን በ100 ግራም የፋብሪካ ምግብ ውስጥ የትራንስ ፋት መጠን ከ2 ግራም እንዳይበልጥ ሀገራት አስገዳጅ ህግ እንዲያወጡ ሲወተውት መቆየቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስነብቧል።
ከልብ ጋር በተያያዙ የጤና እክሎች በ2019 ብቻ 17 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ይህ አሃዝ በቀጣይም ሊጨምር እንደሚችል ያነሳው የአለም ጤና ድርጅት፥ መጥፎ የኮሊስትሮል መጠንን ከፍ የሚያደርጉ ምግቦችን መቀነስ እንደሚገባ አሳስቧል።