ድርጅቱ በአፍሪካ እስካሁን 2 በመቶ የሚሆን ህዝብ ብቻ መከተቡን አስታውቋል
የአለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ላይ ባንዣበበው 3ኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ አስጠንቅቋል፤ አፍሪካም አልተዘጋጀችም ብሏል፡፡ የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ማትሺዲሶ ሞይቲ በሰጡት መግለጫ 3ኛው የኮሮና ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ሲሉ ማስጠንቃቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
3ኛው የኮሮና ወረርሽን እውነትና እየጨመረ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ቫይረሱን ለመከላከል ያለው የመጨረሻ መከላከያ ህክምና ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሯ የአፍሪካ ሀገራት የጥንቃቄ አቅማቸውን በማጠናከር የሆስፒታሎችን መጨናነቅ ማስቀረት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተር ሞይቲ ከሆነ ለአፍሪካ ሀገራት የሚደረገው የክትባት አቅርቦት ወደ መቆም እየቀረበ ነው፡፡
“ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ብዙ ሀገራት አሁን ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን” እየከተቡ ሲሆን ልጆችንም ለመከተብ እያሰቡበት ይገኛሉ ብለዋል ሞይቲ፡፡ ሞይቲ የአፍሪካ ዝግጁ አለመሆንና በክትባት አቅርቦት ላይ ያሉ ማነቆዎች እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሞይቲ ለሆስፒታሎችና እና ለህክምና ሰራተኞች የተሻሉ መሳሪያዎች እንዲኖሩ ጥሪ ቅርበዋል፡፡
ብዙ የአፍሪካ ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች የአደገኛ ህመምተኞች ቁጥር ጭማሪን ለመቋቋም ገና ዝግጁ አይደሉም ብለዋል ሞይቲ፡፡ 24 ከመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በአሁኑ ጊዜ ክትባት የወሰደ ሲሆን በአፍሪካ ግን እስካሁን ድረስ 2 በመቶ የሚሆን ህዝብ ብቻ አንድ ጊዜ መከተቡን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በአፍሪካ ከባለፉት ሁለት ሳምታት ጋር ሲነፃፀር ባለፉት ሁለት ሳምንታት የ 20 በመቶ ጭማሪ አስመዝግባለች ብለዋል ፡፡