የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ቴድሮስ(ዶ/ር) በድርጅቱ ሰራተኞች ሴቶች በመደፈራቸው “አዝኛለሁ” አሉ
በምርመራው መሰረት 20 የድርጅቱ ሰራተኞች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተሳትፈዋል
የአለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች በኮንጎ በነበራቸው ስምሪት ሴቶችን መድፈራቸው በምርመራ ተረጋግጧል ተብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት ኢቦላን ለመከላከል ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ልኳቸው የነበሩ ሰራተኞቹ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል መሳተፋቸው መረጋገጡን አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በዴሞክራቲክ ኮንጎ ለሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎች በአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በመሳተፋቸው ለተጎጅዎች አዝኛለሁ ብለዋል፡፡ ቴድሮስ (ዶ/ር) በዚህ ወንጀል የተሳተፉ ሁሉ ጠያቂ ማድረግ የድርጅቱ የመጀመሪያ ስራ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የምርመራው ውጤቱ በጣም ከባድ መሆኑን ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህ ወንጀል ላይ 20 የሚሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም በኮንጎ ኢቦላን ለመከላከል የተቀጠሩ ባለሙያዎች በዚህ የወንጀል ድርጊት መሳተፋቸው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞኢቲ የተፈጠረው ነገር ልብ ሰባሪ መሆኑን እና በዚህም ማዘናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በኮንጎ ተፈጽሟል ያለውን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በተመለከተ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል፡፡ ሪፖርቱም ኢቦላን ለመከላከል ወደ ስፍራው ያቀኑ ባለሙያዎች ሴቶችን መድፈራቸውንና ሕገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸውን አመልክቷል፡፡
35 ገጾች ያሉት ሪፖርት እንዳመለከተው በፈረንጆቹ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ በርካታ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ ድርጊት የተፈጸመው የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በተላኩ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች እና በሀገሪቱ በተቀጠሩ ባለሙያዎች መሆኑንም የምርመራው ሪፖርት ያመለክታል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታም ከሴቶች አስገድዶ መደፈር ጋር 80 የሚሆኑ ጉዳዮች መቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ሪፖርት መሰረት 20 የዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ እና የስደተኞች ኤጄንሲ ሰራተኞች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል መሳተፋቸው የተገለጸ ቢሆንም ከነዚህ ተቋማት ውጭ ያሉ ድርጅቶች ሰራተኞችም የወንጀሉ ተሳታፊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ለአብነትም የኦክስፋም፣ የወርልድ ቪዥን፣ አሊማ እና ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ሰራተኞች በዴሞክራቲክ ኮንጎ ስቶችን በመድፈር ወንጀል ተሳታፊ እንደሆኑ ይፋ መደረጉን ተገልጿል፡፡