በ2024 ህይወታቸው ያለፈ 5 የእግርኳስ ኮከቦች
ተከላካይ ሆኖ የባሎንዶር ሽልማትን ሁለት ጊዜ በመውሰድ ብቸኛ የሆነው ፍራንዝ ቤከንባወር በ2024 ነው ህይወቱ ያለፈው
ስዊድናዊው አሰልጣኝ ስቬን ጎራን ኤሪክሰንና ብራዚላዊው ማሪዮ ዛጋሎም በዚሁ አመት በሞት ከተለዩ ስፖርተኞች ውስጥ ይገኙበታል
የእግርኳስ አፍቃሪዎች በ2024 በርካታ የሜዳ ላይ ጥበበኞችን ተሰናብተዋል።
ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ በቀረው 2024 ቀድሞ ህይወቱ ያለፈው ብራዚላዊው ማሪዮ ዛጋሎ ነው።
በ92 አመቱ በጀርመን ህይወቱ ያለፈው ማሪዮ ዛጋሎ የአለም ዋንጫን በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ካነሱ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። በ1931 የተወለደው ዛጋሎ 13 ቁጥር የትውልድ አመቱን የመጨረሻ ቁጥሮች ስለያዘች የእድል ቁጥሩ መሆኗን በመጥቀስ 13 ቁጥር መለያን በመልበስ ተጫውቷል።
የጀርመን ብሄራዊ ቡድንና የባየርሙኒክ ፈርጥ ፍራንዝ ቤከንባወርም በ78 አመቱ በሞት የተለየው በጥር ወር 2024 ነበር።
የአለማችን የምንጊዜም ምርጡ ተከላካይ የሚባለው ቤከንባወር ተከላካይ ሆኖ ሁለት ጊዜ የባሎንዶር ሽልማትን በመውሰድ ብቸኛ ነው።
"አጼው" በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ፍራንዝ ቤከንባወር ከዛጋኦ በመቀጠል የአለም ዋንጫን በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት በማንሳት ሁለተኛው ሆኗል፤ ሶስተኛው ፈረንሳዊው ዲዲየር ዴሻምፕ ነው።
ስዊድናዊው ተጫዋችና አሰልጣኝ ስቬን ጎራን ኤሪክሰን በካንሰር በ76 አመታቸው የሞቱትም በዚሁ የፈረንጆቹ አመት ነበር።
ኤሪክሰን የፖርቹጋሉን ቤነፊካ፣ ሮማና ላዚዮን ጨምሮ የተለያዩ የጣሊያን ክለቦችን በእንግሊዝ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ እና ሌስተርን ማሰጠናቸው ይታወሳል።
ከ1977 እስከ 2001 ካሰለጠኗቸው የስዊድን፣ ፖርቹጋል እና ጣሊያን ክለቦች ጋር 18 ዋንጫዎችን ያነሱ ሲሆን፥ ከ2002 እስከ 2006ም የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠናቸው ይታወሳል።
የጣሊያን የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪው ጂጂ ሪቫ እና ሌላኛው የሀገሩ ልጅ ሳልቫቶር ስኪላቺ (ቶቶ) በ2024 ህይወታቸው ካለፉ የእግርኳስ ከዋክብት ውስጥ ይገኙበታል።