ሪያል ማድሪድ - ባርሴሎና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች 2024
ከሪያል ማድሪድ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ እና ላሊጋ ዋንጫን ያነሳው ቪኒሺየስ ጁኒየር በ2024 ለክለቡ 32 ጎሎችን አስቆጥሯል
ለባርሴሎና 40 ጎሎችን ያስቆጠረው ሮበርት ሎዋንዶወስኪ ደግሞ የካታላኑ ክለብ ቀዳሚው ጎል አስቆጣሪ ነው
የፈረንጆቹ 2024 ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩበት ወቅት የስፔን ተቀናቃኝ ክለቦች በላሊጋው ተፋጠዋል።
ሪያል ማድሪድ በ40 ነጥብ ሁለተኛ ፤ ባርሴሎና ደግሞ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ2024 ከሪያል ማድሪድ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ እና ላሊጋ ዋንጫን ያነሳው ቪኒሺየስ ጁኒየር በአመቱ 32 ጎሎችን በማስቆጠር የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኗል።
ከ32ቱ ጎሎች ውስጥ በዌምብሌይ በተካሄደው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በቦርሽያ ዶርትሙንድ ላይ ያስቆጠራትና ሪያል ማድሪድን ለ15ኛው የአውሮፓ ክብር ያበቃችው ተጠቃሽ ናት።
በስፔን ሱፐር ካፕ ፍጻሜ በተቀናቃኛቸው ባርሴሎና ላይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ የሰራውም በ2024 ነበር።
ቪኒሺየስ ጁኒየር የዘንድሮው ባሎንዶር አሸናፊ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም የማንቸስተር ሲቲው ሮድሪ መመረጡ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎችንና አድናቂዎቹን ማስቆጣቱም ይታወሳል።
ፖላንዳዊው የ36 አመት አጥቂ ሮበርት ሎዋንዶወስኪ በላሊጋው 16 ፤ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ 7 ጎሎችን በማስቆጠር በሁለቱም ውድድሮች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው።
ሎዋንዶወስኪ በ2024 በአውሮፓ ሊጎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን ተቃርቧል። የባየርሙኒኩ ሃሪ ኬን 39 ጎሎችን አስቆጥሮ ይከተላል።
ሌላኛው የሎዋንዶወስኪ የቡድን አጋር ራፊንሃ በ24 ጎሎች የባርሴሎና ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ፉክክርን ተቀላቅሏል። ብራዚላዊው ኮከብ በላሊጋው በፈረንጆቹ 2024 አመት 11 ጎሎችን በማስቆጠር የካታላኑ ክለብ ወሳኝ ተጫዋችነቱን አሳይቷል።