51 ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጩ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
ሚኒስቴሩ ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጿል
በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአካልና ዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ዘርግቶ እየመዘገበ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው
51 ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጩ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዛሬው እለት ወደ ሀገራው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን የጦርነት ቀጠና በሆነችው ሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ሥራዎች ቀዳሚ ትኩረቱን በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በተለያዩ ሀገራት ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ቀዳሚ ትኩረቱን በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያስታወቀው።
ቤይሩት የሚገኘው ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤት የዜጎችን ምዝገባ እና ክትትል በተሻለ ፍጥነት ለማካሄድ የሚያስተባብር አመራር ወደ ሊባኖስ ተልኮ ስራ መጀመሩንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
በአሁኑ ወቅትም ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤቱ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአካል እና ዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ዘርግቶ እየመዘገበ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው አክሎም፤ ዜጎች አንጻራዊ ደኀንነት ወደ አለበት የሊባኖስ አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ እንደሚያደርግም ገልጿል።
ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ህጻናት እና ሴቶችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሊባኖስ ዋና ከተማዋ ቤሩትን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በእስራኤል የአየር ላይ ጥቃት ሰለባ መሆኗ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም በሊባኖስ የሚኖሩ ከ30 ሸህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከቀሪው የሀገሪቱ ዜጎች ጋር የደህንት ስጋት ውስጥ ወድቀዋል።