እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ዘመቻ ስታስፋፋ፣ በቤይሩት ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒኤል ሀጋሪ እስራኤል ባደረገችው የእግረኛ ጦር ዘመቻ 400 የሄዝቦላ ተዋጊዎችን መግደሏን ተናግረዋል
የእስራኤል-ሄዝቦላ ግጭት የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራን ወደ ግጭቱ ጎትቶ እንዳያስገባ ተሰግቷል
እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ዘመቻ ስታስፋፋ፣ በቤይሩት ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ።
የደቡባዊ ቤሩት ዳርቻ ከቅዳሜ ምሽት እስከ እሁድ ድረስ በከባድ ፍንዳታ መመታቱን እና ፍንዳታው የፈጠረው እሳት ከብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ይታይ እንደነበር ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ ጥቃት እስራኤል በቤይሩት ከተማ ዳርቻ በሚገኘው የሄዝቦሃ ምሽግ እንደሆነ በሚታመነው ቦታ ላይ በአየር ጥቃት የቡድኑን መሪ ሀሰን ነስረላህን ከገደለች ከቀናት በኋላ የተፈጸመ ነው።
እስራኤል የሄዝቦላ ተተኪ መሪ ይሆናል የተባለውን ሀሽም ሰይፈዲንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት በከተማዋ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ካደረሰችበት ከባለፈው አርብ ጀምሮ ሰይፈዲን የት እንዳለ እንደማይታወቅ ሮይተርስ የሊባኖስን የደህንነት ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ባለፈው መስከረም 27 ነበር የሄዝቦላ መሪ የሆነውን ነስረላህን በቡድኑ ማዕከላዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ በፈጸመው ጥቃት መግዱን ያስታወቀው። ሄዝቦላም ግድያው መፈጸሙን አረጋግጧል።
ባለፈው አንድ አመት ውስጥ እስራኤል በቀጣናው እያደረገች ያለው ጥቃት ባለፉት ሳምንት ጨምራለች፤ በሄዝቦላ አመራሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳለች።
እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ጥቃት እያሳፋፋች ነው። ባለፈው ቅዳሜ ትሪፖሊ በተባለችው ከተማ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ጥቃት መፈጸሟን የሊባኖስ ባለስልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ከተወሰኑ ቦታዎች እንዲለቁ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ቅዳሜ ምሽት በቤይሩት ከተማ ዳርቻ በአየር ማረፊያ አቅራቢያ ጨምሮ ስምንት ፍንዳታዎች መፈጸማቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
እስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ያለው ግጭት በቅርቡ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመድሱ በፊት ከጋዛው ጦርነት ጎን ለጎን በድንበር አካባቢ የተወሰነ የተኩስ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒኤል ሀጋሪ እስራኤል ባደረገችው የእግረኛ ጦር ዘመቻ 400 የሄዝቦላ ተዋጊዎችን መግደሏን እና 2000 የሄዝቦላ ኢላማዎችን ማውደሟን ተናግረዋል። ሄዝቦላ የሟቾቹን ቁጥር ይፋ አላደረገም።
እስራኤል ከድንበር አካባቢ የተፈናቀሉ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጓቿን ለመመለስ በሄዝቦላ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች።
የእስራኤል ባለስልጣናት በደቡባዊ ሊባኖስ በተደረገ ውጊያ ዘጠኝ ወታደሮች ተገድለዋል ብለዋል።
የእስራኤል-ሄዝቦላ ግጭት የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራን ወደ ግጭቱ ጎትቶ እንዳያስገባ ተሰግቷል።