እስራኤል በሊባኖስ ላይ በእግረኛ ጦር ወረራ ጀመረች
የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ መንደሮች በሚገኙ የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ "ውስን፣ አካባቢያዊ እና ኢላማውን የጠበቀ የእግረኛ ጦር ወረራ" መጀመሩን አስታውቋል
እስራኤል በሊባኖስ የእግረኛ ጦር ወረራ ማካሄድ የጀመረው የሄዝቦላ መሪ የተገደለበትን የባለፈው አርቡን ጨምሮ ለሁለት ሳምንታት የአየር ጥቃት ካደገች በኋላ ነው
እስራኤል በሊባኖስ ላይ በእግረኛ ጦር ወረራ ጀመረች።
እስራኤል በሊባኖስ ላይ ታደርገዋለች ተብሎ በስፋት ሲጠበቅ የነበረው የእግረኛ ጦር ወረራ ዛሬ ጠዋት ሲጀምር፣የእስራኤል ጦሩ በድንበር አካባቢ በሚገኙ የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ከፍቷል።
ጦሩ ባወጣው መግለጫ በትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት በደቡብ ሊባኖስ መንደሮች በሚገኙ የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ "ውስን፣ አካባቢያዊ እና ኢላማውን የጠበቀ የእግረኛ ጦር ወረራ" መጀመሩን አስታውቋል።
ጦሩ አክሎም እንደገለጸው አየር ኃይል እና ከባድ መሳሪያዎች ትክክለኛ ኢላማ በመምታት የእግረኛ ጦሩን እየደገፉ ነው ብሏል። ሮይተርስ እንደዘገበው በሊባኖስ የድንበር ከተማ አይታ አል ሻብ የሚገኙ ነዋራዎች ከባድ ተኩስ፣ የሄሊኮፕተር ድምጽ እና ድሮን እያስተዋሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
በትናንትናው እለት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ዩአብ ጋላንት በሰሜን እስራኤል የአካባቢ ለሚገኙ አመራሮች በሊባኖስ ድንበር አካባቢ የሚጀመረው ሁለተኛው የጦርነቱ ምዕራፍ በቅርቡ ይጀመራል ሲሉ ነበር የተናገሩት።
እስራኤል በዚህ ዘመቻ ማሳካት ከፈለገቻቸው ግቦች ዋነኛው በተኩስ የሄዝቦላን የሮኬት ጥቃቶች ሸሽተው የነበሩትን በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሰሜን እስራኤል ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ ነው።
የእግረኛ ጦር ወረራው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰውን የእስራኤል-ሄዝብላ ግጭት ከፍተኛ ጡዘት ላይ አድርሶታል።
እስራኤል በዛሬው እለት ጠዋት ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የፍልስጤሙ ፋታህ እንቅስቀሴ ወታራ ክንፍ የሊባኖስ ቅርንጫፍ አዛዥ የሆነውን ሙኒር መቃህ ኢላማ ማድረጉን ሁለት የፍልስጤም የደህንነት ባለስጣናት ተናግረዋል።
በዚህ የአየር ጥቃት በደቡባዊቷ የሲዶን ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በተጨናነቀ አይን ህልዌህ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ህንጻ ተመትቷል። በሄዝብላ እና እስራኤል መካከል የድንበር ተኩስ ልውውጥ ከተጀመረ ወዳህ ሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ካምፕ ላይ ጥቃት ሲፈጸሞ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
እስራኤል በሶሪያ ደማስቆ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሶስት ንጹሀን መገደላቸውን እና ሌሎች መቁሰላቸውን ሮይተርስ የሶሪያን ሚዲያ ጠቅሶ ዘግቧል። የእስራኤል ጦር በውጭ ሚዲያ ዘገባዎች ላይ መልስ እንደማይሰጥ ገልጿል።
እስራኤል ሶሪያ ውስጥ ባሉ ከኢራን ጋር ግንኙነት ባላቸው ቦታዎች ላይ ጥቃት ስትሰነዝር የቆየች ቢሆንም የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አጠናከራለች።
እስራኤል በሊባኖስ የእግረኛ ጦር ወረራ ማካሄድ የጀመረችው "ፔጀር" በተባለ የሄዝቦላ የመገናኛ መሳሪያ ላይ ፈንጅ አጥምዳ ካፈነዳች እና የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህ የተገደለበትን የባለፈው አርቡን ጨምሮ ለሁለት ሳምንታት የአየር ጥቃት ካደገች በኋላ ነው።
እስራኤል በከፈተችው ከባድ የአየር ጥቃት በርካታ የቡድኑ መሪዎችኝ ማጥፋት ብትችልም 1000 የሚጠጉ ንጹሀን ተገድለዋል።