ኢትዮጵያዊያን በጸሎት እንዲያስቡን እንጂ መንግስት የሚረዳን አይመስለኝም- በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል
ቤሩት ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ በደቡባዊ እና ምስራቃዊ ሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያዊን እንዲመዘገቡ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል
ኢትዮጵያዊያን በጸሎት እንዲያስቡን እንጂ መንግስት የሚረዳን አይመስለኝም- በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስራኤል እና የሊባኖሱ ሂዝቦላህ አዲስ ጦርነት ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሊባኖስ ዋና ከተማዋ ቤሩትን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በእስራኤል የአየር ላይ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በሊባኖስ የሚኖሩ ከ30 ሸህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከቀሪው የሀገሪቱ ዜጎች ጋር የደህንት ስጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን እንዴት እየመሩ ይሆን ሲል የሀገሪቱ መዲና በሆነችው ቤሩትን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ጠይቋል፡፡
ለደህንነቷ በመስጋት ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳለችን ከሆነ ነበለት በሚባለው ቦታ ትኖር እንደነበር ነግራናለች፡፡
በአካባቢው ተከታታይ የእስራኤል የአየር ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ወደ ቤሩት ከአሰሪዎቿ ጋር በመሆን ከተሰደደች አራተኛ ቀኗ መሆኑን ትናገራለች፡፡
“ራሴን እና ቤተሰቦቼን ለመርዳት ወደ ሊባኖስ ከመጣሁ ስምንት ዓመት ሆኖኛል፣ ከስድስት ቀን በፊት የጎረቤታችን ቤት በአየር ሲመታ ሁላችንም ፈርተን ወደ ቤሩት መጣን” የምትለው ይህች አስተያየት ሰጪ ሁኔታው ያስፈራል ብላለች፡፡
ቤሩት ሰላም መስሎን ነበር የመጣነው ሆቴል ውስጥ ነው ከአሰሪዎቼ ጋር ተጠልለን ያለነው፣ አሰሪዎቼ ሆቴል ውስጥ ለረጅም ቀን የሚያቆየን ገንዘብ የለም ሲሉ ሰምቻለሁ ቀጥሎ ምን እንደምንሆን አላውቅም” ስትልም ነግራናለች፡፡
ምን አይነት ድጋፍ ትፈልጊያለሽ? ብለን ላቀረብንላት ጥያቄም “ቤሩት ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ተመዝገቡ ማለቱን ሰምቻለሁ፣ ስንደውል ስልክ አያነሱም፣ ከዚህ በፊት ችግር ገጥሟቸው የተመዘገቡትም ሲረዱ አላየሁም፣ ወደ ሀገሬ መመለሱንም አልፈልግም“ ብላለች፡፡
በቤሩት በአሰሪዎቿ ቤት እየኖረች መሆኗን የነገረችን ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በበኩሏ “ያለሁት በቤሩት ባለ አንድ የመኖሪያ መንደር ውስጥ ነው፣ በህንጻው ላይ ማን እንዳለ አይታወቅም፣ እስራኤሎቹ ታጣቂዎች አሉ ብለው ካመኑ ሙሉ ህንጻውን ይመቱታል፣ ያለው ነገር አስፈሪ ነው“ ስትል ተናግራለች፡፡
“ጦርነቱ ካለባቸው ደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ቤሩት መጥተዋል፣ ህጋዊ ሆነን እየሰራን ያለነው የቻልነውን ያህል ገንዘብ እያዋጠን እየተረዳዳን ነው ግን ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም” ብላለች፡፡
ከአሰሪዎቿ ጋር ሳይዳ ከሚባለው ቦታ ተፈናቅላ በቤሩት ባለ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልላ እየኖረች መሆኗን የነገረችን ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት በበኩሏ የሊባኖስ መንግስት ሳያዳላለሁላችንም ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግራለች፡፡
ይሁንና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ህጋዊ ሆነው እየሰሩ ባለመሆኑ ጎዳና ላይ የወደቁ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ እና የሚረዳቸው እንዳጡም አክላለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ቤሩት ባለው ቆንስላ ጸህፈት ቤት በኩል በቀጣይ ሊደረጉ ለሚችሉ ድጋፎች ተመዝገቡ የሚል ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰምታችኋል? በሚል ላቀረብንላት ጥያቄ ይህን ማስታወቂያ ያልሰማ ሰው የለም ግን ተመዝገቡ የሚባለው የይስሙላ እንጂ የእውነት ለመርዳት አይመስለኝም ብላናለች፡፡
“ከዚህ በፊት ለዓመታት በአሰሪዎቻቸው ገንዘባቸው ያልተከፈላቸው ኢትዮጵያዊያን ተመዝገቡ ተብለው ተመዝግበው መጠለያም ተሰጥቷቸው ነበር አሁን ድረስ እየተንገላቱ ነው” ያለችው ይህች አስተያየት ሰጪ “የሚሻለው ኢትዮጵያዊያን በጸሎታቸው ቢያግዙን እንጂ መንግስት ይረዳናል እሚል ተስፋ የለኝም” ብላለች፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤሩት ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከሶስት ቀናት በፊት በተለይም በደቡባዊ እና ምስራቃዊ ሊባኖስ ያለው የደህንት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጾ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡ ቦታዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ፣ ሁኔታው እየተባባሰ ከሄደ በቀጣይ ለሚወሰዱ እርምጃዎች መረጃዎችን እንዲከታተሉ እና በቤሩት ባለው የቆንስላው አድራሻ እንዲመዘገቡም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ቤሩት ባለው ቆንስላ ጽህፈት በኩል እና በዋናው መስሪያ ቤት በኩል ድጋፍ እንደሚደረግ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡