ለአንድ አመት ያህል በየቀኑ የማራቶን ርቀትን የሮጡት ቤልጄማዊት አዲስ ክብረወሰን አስመዘገቡ
በየቀኑ ከ42 ኪሎሜትር በላይ የሮጡት የ55 አመት ጎልማሳ በአመት ውስጥ ከ15 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ርቀትን ሸፍነዋል
ግለሰቧ ክብረወሰኑን ለመሰብር ያደረጉትን ሙከራ በማህበራዊ ትስስር ገጽ በማጋራት በጡት ካንሰር ላይ ለሚሰራ ድርጅት 65 ሺህ ዩሮ ማሰባሰብ ችለዋል
የ55 አመቷ ቤልጂየማዊት ሂልዲ ዶሶኝ በ2024 366 ሙሉ ማራቶን (ከ15ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ) በመሮጥ በተከታታይ ማራቶን አዲስ የአለም ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል።
ግለሰቧ በሴቶች ዘርፍ ኤርቻና ሙሬይ ባርትሌት በተባለች ሴት ተይዞ የነበረውን የተከታታይ 150 የማራቶን ሩጫ ክብረወሰን በግንቦት 2024 መረከብ ችለው የነበረ ቢሆንም እስከ ፈረንጆቹ አመት መጠናቀቂያ ታህሳስ 31 ድረስ መሮጣቸውን አላቆሙም ነበር።
በአመቱ መጨረሻ በየቀኑ ማራቶንን ለ366 ቀናት በመሮጥ ክብረ ወሰኑን ሲያስመዘግቡ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ በ2023 በብራዚላዊው ሯጭ ሁጎ ፋሪያስ በወንዶች ምድብ ይዞት የነበረውን ክብረወሰን መጋራት ችለዋል፡፡
በየቀኑ 42.195 ኪሜ ለአንድ ዓመት ያህል በተከታታይ መሮጥ ቀላል እንዳልነበር የሚናገሩት ሂልዲ የሚሰማቸውን ከፍተኛ ድካም ፣ የመገጣጠሚያ አጥንቶች ህመም እና የአእምሮ ውጥረትን በማሸነፍ በየእለቱ በመነሻ ነጥብ ላይ መገኝት ፈታኝ ሂደት እንደነበር ያነሳሉ፡፡
ግለሰቧ በቤልጂየም ጌንት ከተማ በሚገኝ የሩጫ ሜዳ 8 ዙር በመሮጥ በእያንዳንዱ ዙር 5 ኪሎ ሜትር ለመሸፈን ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን 42.195 ኪ.ሜ. ለመሙላት ተጨማሪ 2.5 ኪሎ ሜትር እንደሚሮጡ ተናግረዋል፡፡
አስገራሚው ነገር ሂልዲ ዶሶኝ አመቱን ሙሉ ከሩጫው ጎን ለጎን ቋሚ ስራቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን ሩጫውን በማለዳ ከጨረሱ በኋላ ቀጥታ ወደ ስራ እንደሚያመሩ ተሰምቷል፡፡
ለአመት ያህል ሳያቋርጡ ያደረጉት ከፍተኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሰውነታቸው ከፍተኛ ጉልበት እንዲያወጣ ቢያስገድደውም ሰውነታቸውን ለማጠናከር እና አቅም እንዲያገኝ ከምግብ ሳይንስ ባለሙያ ጋር በመነጋገር የተጠና አመጋግብን ይከተሉ ነበር፡፡
ግለሰቧ በሴቶች ተከታታይ ማራቶን አዲስ ክብረ ወሰን ከማስመዝገብ በተጨማሪ ታሪካቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጽ በማጋራት በጡት ካንሰር ላይ ለሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ከ65 ሺህ ዩሮ በላይ እርዳታ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡
የ55 ዓመቷ ሴት ስለ ስኬታቸው ሲገልጹ ክብረወሰኑ የጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ብሩህ ምሳሌ ሳይሆን የግል ጽናት ምሳሌ ተደርጎ እንዲወሰድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡