ቀነኒሳ በቀለ በለንደን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ
በሴቶቹ ተመሳሳይ ውድድር ትዕግስት አሰፋ ኬንያዊቷን የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ጄፕቺርቺር በመከተል ገብታለች
ኬንያ በሁለቱም ጾታዎች ያስመዘገበችው ድል በፓሪሱ ኦሎምፒክ ተስፋዋ እንዲለመልም አድርጓል
በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ኬንያዊው ሙቲሶ ሙንያኦ የ41 አመቱን ቀነኒሳ በቀለ በመቅደም ውድድሩን በ2 ስአት ከ4 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ ማጠናቀቅ ችሏል።
ብሪታንያውያኑ ኢሚል ኬርስ እና ማሀመድ ማህመድ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ውድድሩ ባለፈው አመት አሸናፊ በነበረውና በየካቲት ወር በመኪና አደጋ ህይወቱ ላለፈው ኬንያዊ ኬልቪን ኪፕቱም የህሊና ጸሎት በማድረግ ነው የተጀመረው።
ሙንያኦ የአለም የወንዶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤቱ ኬልቪን ኪፕቱም ጓደኛውና የሁልጊዜም አርአያው መሆኑን በመጥቀስ “ኬልቪን ህይወቱ ቢያልፍም የባለፈውን አመት ድል መድገም በመቻሌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በውድድሩ ያሳየው አይበገሬነትም በስፖርት ቤተሰቡ እየተደነቀ ነው።
በሴቶች የማራቶን ውድድር ኬንያዊቷ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ፒርስ ጄፕቺርቺር አሸንፋለች።
ጂፕቺርቺር ውድድሩ ሊጠናቀቅ 400 ሜትር ሲቀረው የማራቶን ሪከርድ ባለቤቷን ትዕግስት አሰፋ እና ሌሎች ተፎካካሪዎቿን ጥላ በመውጣት ኬንያን በለንደን ያደመቀ ውጤት አስመዝግባለች።
ውድድሩን ያጠናቀቀችበት 2 ስአት ከ16 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስ አሰፋ ካስመዘገበችው የማራቶን ሪከርድ በ4 ደቂቃ ቢዘገይም ያለወንድ አሯሯጭ ከተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ፈጣኑ ስአት ነው ተብሏል።
ከጂፕቺርቺር በአምስት ሰከንዶች የዘገየችው ትዕግስት አሰፋ ሁለተኛ እና መገርቱ አለሙ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ኬንያ በለንደን ያስመዘገበችው ድል ከወራት በኋላ በፈረንሳይ ፓሪስ በሚጀመረው የፓሪስ ኦሎምፒክ በውድድሩ ውጤታማ ልትሆን እንደምትችል አመላካች ነው ተብሏል።