100 ሺህ ዶላር የሚያሸልመው የቺካጎ ማራቶን በኬንያዊያን የበላይነት ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ የማራቶን ሪከርድ በኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ተሰብሯል
ኢትዮጵያዊን በሁለቱም ጾታዎች ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል
100 ሺህ ዶላር የሚያሸልመው የቺካጎ ማራቶን በኬንያዊያን የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡
የቺካጎ ማራቶን ውድድር በዓለማችን ካሉ ተጠባቂ የማራቶን ርቀት ውድድሮች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለአሸናፊነት በተጠበቁበት በዚህ ውድድር ላይ ኬንያዊያን በሁለቱም ጾታዎች የበላይ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
ሩት ቼፕንጌቲች ውድድሩን 2፡04፡50 በሆነ ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆና ከማጠናቀቋ ባለፉ በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን የማራቶን ሪከርድ የግሏ ማድረግ ችላለች፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ለአንደኝነት ስትጠበቅ የነበረችው ሱቱሜ ከበደ ሁለተኛ እንዲሁም ሌላኛዊ ኬንያዊት ኢሬኔ ቼፔት ደግሞ ሶተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር ኬንያዊው ጆን ኮሪር ውድድሩን 2፡02፡44 በሆነ ሰዓት አንደኛ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ሞሀመድ ኢሳ ደግሞ ሁለተኛ ሲወጣ ሌላኛው ኬንያዊ አሞስ ከፕሩቶ ሶተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
አትሌት ጆን ኮሪር የቺካጎ ማራቶንን ከሁለት ዓመት በፊት በአንደኝነት አጠናቆ ነበር፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የተካሄደው የ2023 ቺካጎ ማራቶንን ከወራት በፊት በትራፊክ አደጋ ህይወቱ ያለፈው ኬልቪን ፒፕቱም የማራቶንን ሪከርድ በመስበር ጭምር በአንደኝነት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
የቺካጎ ማራቶን ውድድርን አንደኛ ለወጣ 100 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት የሚያስገኝ ሲሆን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ለወጡ ደግሞ 75 ሺህ እና 50 ሺህ ዶላር ሽልማት ያስገኛል፡፡