በፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድሩን እንዳጠናቅቅ ያደረገኝ የሀገሬ ፍቅር ነው - አትሌት ቀነኒሳ
አትሌቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ከከባድ ጉዳት ጋር ታግሎ ውድድሩን ማጠናቀቁን አውስቷል
የቤጂንግ ኦሎምፒክ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ሻምፒዮኑ ኦሎምፒክ የአይበገሬነት ማሳያ መድረክ ጭምር መሆኑን ገልጿል
በፓሪስ ኦሎምፒክ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ጉዳት አጋጥሞት እንደነበር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ገለጸ።
አትሌቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ለፓሪስ ኦሎምፒክ ለራሴ ምርጥ ነው ያልኩትን ዝግጅት አድርጌ ነበር ብሏል።
“ከባድ የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ገጠመኝ፤ 10 ኪሎሜትሮችን እንደሮጥን ህመሙ እየባሰ መጣ፤ 15 ኪሎሜትር ላይ ለማቋረጥ እያሰብኩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ለሀገሬ ኢትዮጵያ ያለኝ ፍቅር ከነጉዳቴ ውድድሩን እንዳጠናቅቅ ገፋፋኝ” ሲልም ገልጿል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ኦሎምፒክ ሜዳልያ የማግኘት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነም ነው ያነሳው።
ግዙፉ መድረክ ለአለም አይበገሬነትን እና ቆራጥነትን የምናሳይበት ነው ብሏል።
አትሌቱ ከገጠመው ጉዳት እያገገመ መሆኑንና ተስፋ እንደማይቆርጥ በመጥቀስም ድጋፍ ለቸሩት ኢትዮጵያውያን እና ለመላው አድናቂዎቹም ምስጋናውን አቅርቧል።
የ42 አመቱ ቀነኒሳ በቀለ በፓሪስ ኦሎምፒክ 39ኛ ደረጃን ይዞ ቢያጠናቅቅም ውድድሩን ለማጠናቀቅ ያይሳየው ብርታት አርአያ የሚሆን ነው በሚል ሲወደቅ መቆየቱ ይታወሳል።
በ2019 በበርሊን ኦሎምፒክ 2 ስአት ከ1 ደቂቃ ከ41 ስአት በመግባት ያሸነፈው ቀነኒሳ በቀለ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ለሀገሩ ያስገኘ አትሌት ነው።
በቀጣይም ከጉዳቱ አገግሞ ወደለመደው ድል እንደሚመለስ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው መረጃ ይጠቁማል።