በ6 አመቷ ቪዲዮ ጌም የሰራችው ህጻን በድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን አስፍራለች
ካናዳዊቷ ሲማር ኩራና እምደ እኩዮቿ ጌም መጫወትን ሳይሆን መስራትን መርጣ በብዙ ጥረት አሳክታዋለች
ሲማር የሰራችው ጌም ህጻናትን እያዝናና ስለጤናማ አመጋገብ የሚያስተምር ነው ተብሏል
የህጻናት እና ታዳጊዎች የስማርት ስልክ አጠቃቀም በየጊዜው የመጨመሩ ነገር አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት የስድስት አመቷ ካናዳዊ ህጻን በፈጠራ ብቅ ብላለች።
እንደ እድሜ እኩዮቿ በስማርት ስልኮች የቪዲዮ ጌሞችን ሲጨወቱ ከመዋል ጨዋታውን በራሷ መስራትን መርጣለች።
ሲማር ኩራና በለጋ እድሜዋ የቪዲዮ ጌም በመስረት ስሟን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ ማስፈር ችላለች።
ባለፈው አመት የኮዲንግ ትምህርት የጀመረችው ሲማር በሳምንት ሶስት ክፍለጊዜ የሂሳብና ኮዲንግ ትምህርቷን ስትከታተል መቆየቷን አባቷ ይናገራሉ።
“የመዋዕለ ህጻናት ተማሪ እያለች የሶስተኛ ክፍል ተማሪዎችን የሂሳብ ፈተናዎች መስራት ትችል ነበር፤ ከወረቀትም ሆነ ከወዳደቀ ነገር ቅርጻ ቅርጾችን መስራት ታዘወትራለች” ሲሉም ያክላሉ።
ፍላጎትና አቅሟን ያጠኑት አባት ሲማርን ወደ ኮዲንግ ትምህርት ቤት እንዳይልኩ እድሜዋ ያግዳታል፤ መምህር ቀጥረውላት በቤት እንድትማር ያደረጉት ጥረትም ረጅም ጊዜ ወሰደባቸው።
ከወራት በፊት መምህር ተገኝቶላት በሳምንት ለአራት ጊዜ እስከ 2 ስአት የሚወስድ ስልጠና ስትወስድ የቆየችው ሲማር ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ሆስፒታል ባመራችበት ወቅት ከዶክተሩ የሰማችው ምክር የፈጠራዋ መነሻ ሆነ።
የህክምና ባለሙያው ለእሷ እና እህቷ ከጣፋጭና በፋብሪካ ከተቀነባበረ ይልቅ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ ምግቦችን እንዲያዘወትሩ ነበር የመከራቸው።
ሲማርም ይህንኑ ሃሳብ ወደ ቪዲዮ ጌም ቀይራው የእድሜ እኩዮቿ ጤናማውን የጎንዮሽ ጉዳት ካለው የምግብ አይነት እየተዝናኑ እንዲለዩና እንዲማሩበት ማድረግ ችላለች።
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለመስፈር ከመደበኛ ትምህርቷ ጎን ለጎን በአራት ወራት ውስጥ አሳየችው የተባለው ቁርጠኝነት የወደፊት ተስፋውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት የጀመረችው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስልጠናም ሲማር ኩራና አዳዲስ የአለም ሪከርዶችን ለመያዝ እየሰራሁ ነው ብላለች።