ለቀናት አድካሚ ሙከራ አድርገው በድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸውን ያሰፈሩ ግለሰቦች እነማን ናቸው?
ናይጀሪያቷ ሼፍ ሂልዳ ባሲ ለ93 ስአት ምግብ በማብሰል የአለም ክብረወሰንን ሰብራለች
የሂልዳን አነጋጋሪ ሪከርድ ተከትሎ በየዘርፉ ረጅም ስአት ወስደው በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸውን ያሰፈሩ ሰዎች ዝርዝር ወጥቷል
በአለም የድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸውን ለማስፈር በርካቶች መስዋዕትነት ይከፍላሉ።
መስዋዕትነቱ በቀላል ድካም ሊያልፍ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በሰውነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ጉዳትን ይዞ ሊመጣ ይችላል።
በቅርቡ ለረጅም ስአት ምግብ በማብሰል የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሟን ያስፈረችው ናይጀሪያዊቷ ሂልዳ ባሲም ከነዚህ ሰዎች መካከል ናት።
ሂልዳ ለ93 ስአት ከ11 ደቂቃ ምግብ በማብሰል ከዚህ ቀደም በህንዳዊቷ ላታ ቶንዶን ተይዞ የነበረውን (87 ስአት ከ45 ደቂቃ) ሪከርድ ሰብራለች።
የሂልዳን የማራቶን የምግብ ማብሰል ሪከርድ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች ለረጅም ስአት የወሰዱ ድንቃድንቅ ጉዳዮች እየተጋሩ ነው።
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብም በድረገጹ በመጽሃፉ ስማቸውን ለማስፈረ ለረጅም ስአታት ትግል ያደረጉ ሰዎችን በየዘርፉ ይፋ አድርጓል።
- ለረጅም ስአት ጊታር የተጫወተ - ዴቪድ ብራውን (አየርላንድ) – 114 ስአት ከ6 ነጥብ 30 ደቂቃ
- ለረጅም ስአት ፍሉት (ዋሽንት) የተጫወተች - ካትሪን ብሩክስ (ብሪታንያ) – 27 ስአት ከ32 ነጥብ 32 ደቂቃ
- ለረጅም ስአት ዶጅቦል የተጫወተ ቡድን - ራይት ቱ ፕሌይ አት ካስቴሎን (አሜሪካ) – 41 ስአት ከ3 ነጥብ 17 ደቂቃ
- ለረጅም ስአት ስዕል የሳሉ - ሮላንድ ፓልመርትስ (ቤልጂየም/ካናዳ) – 60 ስአት
- ለረጅም ስአት ጮክ ብሎ መጽሃፍ ያነበበ- ሪይስባይ ኢሳኮቭ (ኪርጊስታን) – 124 ስአት
- ለረጅም ስአት ስጋ የከተፈ - ቦኒሎ ራሞስ (ስፔን) – 72 ስአት 13 ነጥብ 8 ደቂቃ
በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ለመስፈር ረጅም ስአትን ወስደው የሚሞክሩት በርካቶች ቢሆኑም የሚሳካላቸው ጥቂቶች ናቸው።
ለዚህም የአለም ድንቃድንቃ መዝገብ የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መጣሳቸው አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል።
በእያንዳንዱ የክብረወሰን የመስበር ረጅም ሙከራ በአንድ ስአት ውስጥ 5 ደቂቃ ብቻ ማረፍ ይፈቀዳል።