በ92 አመታቸው ማራቶን ያጠናቀቁት አዛውንት በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን አሰፈሩ
አሜሪካዊቷ ማቲያ አለንስሚዝ 42 ነጥብ 1 ኪሎሜትሩን በ10 ስአት ከ48 ደቂቃ በማጠናቀቅ ታሪክ ሰርተዋል
በ46 አመታቸው ሩጫ የጀመሩት አዛውንቷ አዳዲስ ክብረወሰን ለመስበር ልምምዳቸውን ቀጥለዋል
በ92 አመታቸው የማራቶን ውድድርን ያጠናቀቁት አዛውንት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸውን ማስፈር ችለዋል።
ማቲያ አለንስሚዝ የተባሉት አሜሪካዊት በሀዋይ የተደረገ የማራቶን ውድድርን በ10 ስአት ከ48 ደቂቃ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ እውቅና የሰጣቸው።
በሳምንት ለስድስት ቀናት እንደሚሮጡ የሚናገሩት ማቲያ፥ ከ46 አመታቸው ጀምሮ ሩጫን የሙጥኝ ብለው ይዘውታል።
በቀን 3 ኪሎሜትር መሮጥ ለጤና ወሳኝ መሆኑ ከጓደኛቸው የተነገራቸው አዛውንቷ ከፈረንጆቹ 1977 ጀምሮ በሳምንት ቢያንስ 60 ኪሎሜትሮችን እንደሚሮጡ ገልጸዋል።
የእድሜያቸውን ግማሽ የሚሆን ጊዜ በሩጫ ማሳለፋቸውም ሸንቃጣ አቋምና ጤናን እንዳላበሳቸው ነው የሚናገሩት።
በ1982ቱ የቦስተን ማራቶን የጀመሩት ማቲያ፥ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የሚወስድባቸው ጊዜ ከአትሌቶች እጅግ ስለሚዘገይ የስታዲየም በሮች እንደሚዘጋባቸው ያወሳሉ።
ባለፈው አመት በሃዋይ በተደረገው የሆኖሉሉ ማራቶን ግን የስታዲየም በሮች ባለመዘጋታቸውና ውድድራቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከውድድሩ አሸናፊዎች አምስት እጥፍ ዘግይተው ቢያጠናቅቁም የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ማራቶንን ያጠናቀቁ አዛውንት ብሎ እውቅና እንደሰጣቸው ትናንት በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
አዛውንቷ በቀጣይም የግማሽ ማራቶን እና 10 ሺህ ሜትር ውድድርን ያጠናቀቁ አዛውንት ተብለው ስማቸው በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ልምምዳቸውን መቀጠላቸውን ነው የተናገሩት።
ማቲያ “አብዛኛውን ጊዜዬን መንገድ ላይ ነው የማሳልፈው፤ በየቀኑ እሮጣለሁ፤ ሩጫና ጤና ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው” ይላሉ።
በእድሜ መግፋትም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚፈጠር ጭንቀትን ማስወገጃው ሁነኛ መፍትሄም እንቅስቃሴ ማድረግ ስለመሆኑ ከ46 አመት ተሞክሯቸው አጋርተዋል።