በ2022 በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የሰፈሩ አስገራሚ ጉዳዮች
በዚህ የፈረንጆቹ አመት አለምን አጃኢብ አስብለው ከሰፈሩት ውስጥ ባለ ረጅም እግሯ እንስት እና ጺማሞቹ አሜሪካውያን አይዘነጉም
ረጅሙ የዱባ ጀልባ ጉዞ እና በጃፓን ትልቁ የሞክሼዎቹ ስብስብም በዚህ አመት በድንቃድንቅ መዝገብ ከሰፈሩት መካከል ይጠቀሳሉ
በፈረንጆቹ 1955 ጥቅምት 5 መታተም የጀመረው የአለም የድንቃድንቅ መጽሃፍ ከ40 ሺህ በላይ የመዘገባቸው ክብረወሰኖች አሉ።
ይሁን እንጂ በየአመቱ እያተመ የሚያወጣቸው ከ4 ሺህ እንደማይበልጡ ይነገራል።
ሊገባደድ የቀናት እድሜ የቀረው የፈረንጆቹ 2022ም በርካታ ክብረወሰኖች የተሻሻሉበት መሆኑን ዩፒአይ በዘገባው አስፍሯል።
በዚሁ አመት በድንቃድንቅ መዝገቡ ከሰፈሩት ውስጥ የተወሰኑትን እነሆ፥
ፈጣኑ የሚያነድ ቃሪያ ተመጋቢ
ግሪጎሪ ፎስተር በማቃጠል ደረጃው የአለማችን ቁንጮ የሆነውን 10 የካሮሊና ቃሪያ በ33 ነጥብ 15 ሰከንዶች በመመገብ ክብረወሰኑን ይዟል።
“ሆደ ብረቱ” የሚል ቅጽል ስም የወጣለት የካሊፎርኒያ ነዋሪ በ2021 ሶስት አፍን የሚያነዱ ቃሪያዎችን በ8 ነጥብ 72 ሰከንድ ቆርጥሞ በመብላት በድንቃድንቅ መዝገብ መስፈር ችሎ ነበር።
ትልቁ የሞክሼዎች ስብስብ
ጃፓናውያን መልካቸው ብቻ ሳይሆን ስማቸውም ይመሳሰላል።
ለዚህም ይመስላል የጃፓናውያን የሞክሼዎች ማህበር በ1994 የተመሰረተው።
በ2022 ጥቅምት ወር መዲናዋ ቶኪዮ ያስተናገደችው ሁነትም በድንቃድንቅ መዝገብ ስፍሯል።
178 ሂሮካዙ ታናካ የሚል ስያሜን የሚጋሩ ሰዎች የተገናኙበት መድረክ በአይነቱ ልዩ ሆኖ ተመዝግቧል።
በ2005 በዚያው በጃፓን ማርታ ስቲዋርት የሚል ስም ያላቸው 164 ሰዎች ተሰባስበው አዲስ ክብረወስን መያዛቸው የሚታወስ ነው።
ሪከርድ የሚሰባብረው ራሽ
ክብረወሰኖችን በመሰባበር የሚታወቀው ዴቪድ ራሽ 250ኛ የአለም ድንቃ ድንቃድንቅ ክብረወሰን ያስመዘገበው በ2022 ነው።
በ2021 በ52 ሳምንት ውስጥ 51 ሪከርዶችን ያሻሻለ ራሽ አንድ ጊዜ ብቻ ተንፍሶ ወለል ላይ የተቀመጠች የአተር ፍሬን ከ25 ሜትር በላይ በመግፋት አዲስ ክብረወሰን ይዟል።
የአሜሪካ የተሰጥኦ ውድድሮች እና የምሽት የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ በተደጋጋሚ የቀረበው ዴቪድ ራሽ በ2023ም አግራሞትን በሚጭሩ ስራዎች ይጠበቃል።
በዱባ ጀልባ ረጅሙ ጉዞ
ዱዋን ሃንሰን የተባለው አሜሪካዊ 60ኛ አመት የልደት በዓሉን በተለየ መንገድ አክብሮታል።
ሃንሰን ከግዙፍ ዱባ ያዘጋጃትን ጀልባ በሚዙሪ ባህር እየቀዘፈባት ያለፈበትን የህይወት ውጣ ውረድ ማብሰልሰል ይዟል።
እንደ ቀልድ የጀመረው ጉዞ ግን ለ11 ስአት ቀጥሎ ኔብራስካ ከተማ ደረሰ።
አሜሪካዊው 60 ኪሎሜትሮችን በዱባ ጀልባ በመጓዝም ስሙን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ማስፈር ችሏል።
ጢማሞቹ
በአሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ዋዮሚንግ ከተማ የተሰባሰቡ ሪዛሞች የትብብርን ሃይል አሳይተዋል።
እርስ በርስ የተጋመደው ጢም ሲለካ 45 ሜትር በመሆኑም አዲስ ክብረወስን ሆኖ ተመዝግቧል።
የለስላሳ ጠርሙሶችን በፊቱና በጭንቅላቱ አጣብቆ የሚይዘው
ከልጅነቱ ጀምሮ ፊቱ ቁሶችን የመሳብ አቅማቸው ከፍ ያለ መሆኑን የሚናገረው የዊስኮንሲን ነዋሪው ጃሚ ኬተን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2016 ስምንት የለስላሳ ጠርሙሶችን ፊቱ ላይ አጣብቆ በመቆየት የአለም ክብረወሰንን ይዟል።
በ2019 ጭንቅላቱ ላይ 9 ጠርሙሶችን በያዘው ጃፓናዊ ሪከርዱ የተሰበረበት ኬተን በ2022 ዳግም ክብረወሰኑን ጨብጦ ስሙን በድንቃድንቅ መዝገብ አስፍሯል።
ጠርሙሶቹ በኬተን ፊትና በተላጨው ጭንቅላቱ የሚቆዩት ለአምስት ሰከንዶች ነው።
ተሰባሪውን እንቁላል የማይፈራው ኢራቃዊ
በአንድ እጃችሁ ስንት እንቁላል መያዝ ትችላላችሁ? በመዳፋችሁ ሳይሆን በጀርባው
ኢብራሂም ሳዲቅ የተባለው ኢራቃዊ ግን 18 እንቁላሎችን በአንድ እጁ ጀርባ ሚዛናቸውን ስተው እንዳይወድቁ አድርጎ በመያዝ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሙን ማስፈር ችሏል።
“ከዚህ ስኬት ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ትኩርትና ትንፋሽን መሰብሰብ ያስፈልጋል፤ ከባድ ጫናው የሚፈጥረውን ህመምም መታገስ የግድ ነው” ብሏል ኢብራሂም።
ረጅሙ የገመድ ላይ ጉዞ
ከሁለት አመቷ ጀምሮ በሰርከስ ቡድን ስትስራ የቆየችው አሜሪካዊ በግንቦት ወር 2022 የድካሟ ፍሬን አጣጥማለች።
የቬርሞንቷ አሪያና ዉንደርሊ 10 ሴንቲሜትር የሚረዝም ሂል ጫማ አድርጋ በገመድ ላይ 194 ሜትሮችን ተጉዛ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግባለች።
ሩስያዊቷ ኦክሳና ሴሮሽታን በ2014 14 ሜትር ገመድ ላይ በመራመድ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በእጅጉ ያሻሻለችው ዉንደርሊ በ2022 ስማቸውን በድንቃድንቅ መዝገቡ ካሰፈሩት መካከል አንዷ መሆን ችላለች።