በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተመድ ዕውቅና ተሰጠው
643 የሰላም አስከባሪ አባላት በደቡብ ሱዳን ለነበራቸው ተሳትፎ ነው ዕውቅና የተሰጣቸው
የኢትዮጵያ ወታሮች የጎሳ ግጭቶችን እንዲቀንሱና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲኖር ደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር- ተመድ
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ የተሰማሩ ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባሎች ለነበራቸው አስተዋጽኦ የድርጅቱ ሜዳሊያ ተበረከተላቸው።
ተልዕኮው እንዳስታወቀው 643 የሰላም አስከባሪ አባላት በአዲሷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ለነበራቸው ተሳትፎ ነው ዕውቅና የተሰጣቸው፡፡
የኢትዮጵያ ወታሮች በደቡብ ሱዳን የጎሳ ግጭቶችን እንዲቀንሱ፤ የብቀላ ጥቃቶች እንዳይኖሩ፤ ማህበረሰቡ እምነት እና በራስ መተማመን እንዲኖረው ማድረጋቻን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲኖር ደረጉት አስተዋጽኦ በምንም የማይለካ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል።
ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል ሻለቃ ወንድማገኝ አርአያ ሁኔታዎቹ አስቸጋሪ እንደነበሩ ገልጸው፤ በቀጥታ ግጭቱ ባለበት ቦታ በመግባት የማረጋጋት ስራ ሲሰሩ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት፤ ንጹሃንን በመጠበቅ የሚጠበቅባቸውን ማድረጋቸውን ሻለቃ ወንድማገኝ ገልጸዋል።
በጆንግሌይ እና በታላቁ ፒቦር አስተዳደራዊ አካባቢ የነበረው ሁኔታ ቀላል እንዳልነበር የገለጹት ኢትዮጵያውያኑ፤ በአካባቢዎቹ የነበረው መልከዓ ምድርና የአየር ሁኔታው አድካሚ እንደነበር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፤ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከዓለም አቀፍና ከአካባው ሀገራት ጋር በመሆን ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረጓን ተመድ ገልጿል።