በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል የሚወጣ ከሆነ ለከፈለው መስዋዕትነት ክብር ተሰጥቶት ሊሆን ይገባል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሱዳን በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲወጣ መጠየቋ ይታወሳል
10 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን በ35 በረራዎች ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል
በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል ቦታውን ለቆ የሚወጣ ከሆነ ለከፈለው መስዋዕትነት ተገቢውን ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በመስጠት ላይ ናቸው።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በአብዬ ግዛት የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሀይል ለከፈለው መስዋዕትነት ተመድ ምስጋና ማቅረቡን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሀላፊ ጋር በተወያዩበት ወቅት ተናግረዋል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት አቶ ደመቀ መኮንን ውይይት ያደረጉት ከተመድ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ፣ የሰላም ግንባታ ጉዳዮች እና ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ግርሃም ሜይትላንድ ጋር ነው።
ሱዳን በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲወጣ መጠየቋ ይታወሳል።ኢትዮጵያ ደግሞ ውጡ ከተባለም ዕውቅና ተሰጥቶ መሆን አለበት ብላለች።
የሰላም አስከባሪ አባላት ጥገኝነት መጠየቃቸው አግባብ አይደለም ሲሉ አቶ ደመቀ ገልጸውላቸዋል ።
አቶ ደመቀ መኮንን በአብዬ የሰላም ማስከበር ዙሪያ ከተመድ የስራ ኃላፊ ጋር በተወያዩበት ወቅት አብዬ ስላለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
ውይይቱ በአብዬ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ስትራቴጂክ ግምገማና በተልዕኮውን መልሶ ማዋቀር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
በወቅቱም አቶ ደመቀ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ በአብዬ ግዛት መቆየት እንዳለበት መናገራቸው ተገልጿል።ሃይሉ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲወጣ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡
የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ከስፍራው መውጣት በአካባቢው ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ግጭት እንደሚያባብሰውም ገልፀዋል።
ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከአብዬ ግዛት እንዲወጣ ያቀረበችውን ጥያቄ በተመለከተም፥ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በደረሱት ስምምነት መሰረት በተመድ ስር በስፍራው መሰማራቱን አስረድተዋል፡፡
አቶ ደመቀም የኢትዮጵያ ወታደሮች ጦርነትን ለመከላከል ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን አንስተው፣ መውጣታቸው አስፈላጊ ከሆነም በባለድርሻ አካላት አስፈላጊው መግባባት ተደርሶበት እና ተገቢውን ክብር በጠበቀ ሁኔታ መሆን እንደሚገባ መናገራቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቃል አቀባዩ በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በተጀመረው ዘመቻ መሰረትም እስካሁን በ35 በረራዎች 9ሺ 902 ዜጎች መመለሳቸውን ተናግረዋል።