ተመድና የአፍሪካ ሕብረትበዳርፉር ያሰማሩት የሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ ተጠናቀቀ
በሱዳን ዳርፉር ግጭት እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ 300 ሺ ሰዎች እንደተገደሉ ይታመናል
የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ በመጠናቀቁ በዳርፉር ተቃውሞ ተቀስቅሷል
ወደ ሱዳን ዳርፉር ከ13 ዓመታት በፊት የተላከው የተመድና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር የሰላም አስከባሪ ኃይል ለቆ እንዲወጣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተወስኗል፡፡
የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት በዳርፉር ያሰማሩት የሰላም አስከባሪ ኃይል (ዩናሚድ) ባወጣው መግለጫ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ሲወጣ የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መንግስት ጸጥታ እና ደህንነት ለማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጿል፡፡
15 ቋሚና ተለዋጭ አባላት ያሉት የጸጥታው ምክር ቤት በዳርፉር ያለው የመንግስታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ ዛሬ ፣ በአውሮፓውያኑ 2020 የመጨረሻ ቀን እንዲያበቃ ፣ በሙሉ ድምጽ የወሰነ ሲሆን ከውኔው በኋላ በዳርፉር ተቃውሞ መነሳቱን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የሰላም አስከባሪ ኃይሉ እስከ ሰኔ 30 ጠቅልሎ እንደሚወጣ የሚጠበቅ ሲሆን በሱዳን ጸጥታ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሰሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጂ ፣ የሱዳን የጸጥታ ኃይል የዳርፉር ንጹሃንን ለመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰዱን ገልጸው ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ከጎኗ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ዳርፉርን ለቆ እንደሚወጣ ከተገለጸበት ዕለት ጀምሮ በአካባቢው የተቃውሞ ሰልፍ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን በዚህም የንጹሃን ህይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
የጥምር የሰላም አስከባሪ ኃይሉ 4ሺ 50 ወታደራዊ መኮንኖች፣ 2ሺ 500 የፖሊስ አማካሪዎችና የሰለጠኑ ፖሊሶችን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት በጎ ፈቃደኛ ሰራተኞችን እና ሌሎችንም ያካተተ ነው፡፡
በዳርፉር ላለፉት 13 ወራት በሰላም አስከባሪነት ያገለገሉ ወታደሮችን ያዋጡ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ሩዋንዳ ፣ፓስታን፣ግብጽ፣ታንዛኒያ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ቻይና፣ ኔፓል፣ ባግላዲሽ፣ ጋምቢያ፣ናይጀሪያ፣ ኬንያ እና ሴኔጋል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ከወታደሮች በተጨማሪም የፖሊስ አባሎችንም አዋጥተዋል፡፡
ከአውሮፓውያኑ 2003 ጀምሮ በአማጺያን እና በሱዳን ጦር መካከል በተደረገው ውጊያ በዳርፉር 300 ሺ ሰዎች እንደተገደሉ እና 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ይታመናል፡፡