”የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ መተናኮል ለሱዳን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንባታል” አምባሳደር ዲና
ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ሌላ አደራዳሪ እንደማትፈልግ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል
ሱዳን ከጥቅምት 27 በፊት ወደነበረችበት ሳትመለስ ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ለድርድር እንደማትቀመጥ አምባ. ዲና በድጋሚ አረጋግጠዋል
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ አንዳንድ ሀገራት አዲስ አበባን እና ካርቱምን ለማደራደር እየጠየቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ ወደ ድርድር የምትሄደው ሱዳን ከጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት ወደነበረችበት ቦታ ስትመለስ መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል፡፡
አላስፈላጊ ግጭት መፈጠሩ ያሳሰባቸው ወገኖች እናደራድራችሁ ማለታቸውወን ኢትዮጵያ እንደምታመስግን የገለጹት ቃል አቀባዩ ፣ ኢትዮጵያ ለድርድር ዝግጁ ብትሆንም ባስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ መጽናቷን አስታውቀዋል፡፡ “ወደነበራችሁበት ተመለሱና ወዲያውኑ እንነጋገራለን፤ በደቂቃዎች ውስጥም ድርድር እንጀምራለን ብለናቸዋል“ ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን ያስተላለፈውን መልዕክት ገልጸዋል፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 18/2021 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ከሱዳን ጀርባ የሶስተኛ ወገን ፍላጎት እንዳለ መግለጹን ያወሱት አምባሳደር ዲና ፣ አዲስ አበባ ሶስተኛ ወገን አለ የምትልበት ምክንያት ሱዳን የድንበር ውዝግቡ በቆየባቸው በ100 ዓመት ውስጥ አድርጋው ወደማታውቀው ጉዳይ በመግባቷ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሱዳን በዚህ ሰዓት እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ መግባቷ እንዳሳዘናት ኢትዮጵያ መግለጿ የሚታወስ ሲሆን ይህም የሌላ ሀገር ፍላጎት እንዳለ ያመለክታል ነው ያሉት፡፡ ምንም እንኳን “ሱዳን ለሰላም ፍላጎት ባታሳይም” አሁንም “ኢትዮጵያ ጉዳዩ በሰላም ይፈታል” ብላ እንደምታምን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ “ችግሩ ቀደም ሲል በነበረው የሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይ የሚፈታበት መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት አለን” ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ እምነት እንደሌላት መግለጿን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አምባሳደር ዲና “የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ መተናኮል ለሱዳን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንባታል” ብለዋል፡፡ ይህ የሱዳን ተግባር ለሰላም ከቆሙ ኃይሎች ጋር እንደሚያጋጫትም ነው ያነሱት፡፡
ሕዳሴ ግድብ
ሱዳን ባለፈው ሳምንት ባወጣችው መግለጫ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና እና የአውሮፓ ህብረት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ፍላጎት እንዳላትና ለዚህም ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ሌላ አደራዳሪ እንደማትፈልግ ገልጻለች፡፡ “ሌላ አሸናጋይ አንፈልግም ፤ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን እንዲፈታ በሚለው መርህ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመሆኗ ጉዳዩ በሷ ብቻ እንዲታይ እንሻለን ብለዋል” አምባሳደር ዲና፡፡
ትግራይ ክልል
በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ማድረግ የሚስችል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ አሁኑ ላይ ከ75 በላይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት ትግራይ ላይ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ቶሎ ለማድረስ በክልሉ 36 ወረዳዎች በተቋቋሙ 92 የዕርዳታ መስጫ ጣቢያዎች በኩል ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት የቆየና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያን መንግስት ቋሚ አቋም አንስተዋል፡፡ ይሁን እና አዲስ አበባ ከቀድሞው የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ያላት ግንኙነት ፣ በተለይ ወደመጨረሻ አካባቢ ጥሩ እንዳልነበር የገለጹ ሲሆን ከአዲሱ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት ግን የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት መነሻ ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረው የድጋፍ ቅነሳ ከሕዳሴው ግድብ ጋር መያያዙ እንደሚቆም መግለጿ”የሚደነቅ ውሳኔ ነው” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፡፡