የ16 አመት ታዳጊ ባገቡ ማግስት አማታቸውን የሾሙት ከንቲባ ሊከሰሱ ነው
የ65 አመቱ ከንቲባ የሚስታቸውን እናት የባህልና ቱሪዝም ሃላፊ አድርገው ሾመዋል
ከንቲባው ለቀረበባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ “የ26 አመት ልምድ ያላቸውን” (አማታቸውን) ባለሙያ መሾም ምንም አያስወቅስም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል
በብራዚል በ49 አመት የሚበልጧትን የ16 አመት ታዳጊ ያገቡት ከንቲባ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነው ሰንብተዋል።
የ65 አመቱ ከንቲባ በጋብቻው ማግስት አማቻቸውን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አድርገው መሾማቸውም በትንግርት ላይ ትንግርት ፈጥሯል።
በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ወላጆች እስከፈቀዱ ድረስ የ16 አመት ታዳጊ ጋብቻ መፈጸም ትችላለች።
በሀገሪቱ ፓራና በተሰኘችው ግዛት የአሩዋካሪያ ከተማ ከንቲባም ይህንኑ ህጋዊ ድጋፍ ተጠቅመው በ49 አመት የሚበልጧትን ታዳጊ ለጋብቻ ጠይቀው ወላጆቻቸው ይሁንታ ሰጥተው ተጋብተዋል።
ያለእድሜ ጋብቻው መነጋገሪያ መሆኑ ሳይበርድ የሰጡት ሹመትም በመላው ብራዚል ትልቅ ርዕሰ ወሬ ሆኗል ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
የ65 አመቱ ሂሳም ሁሴን ዴሃኒ ለአማታቸው የከተማዋን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊነት ሹመት ሰጥተዋል።
ሹመቱን የሙስና ድርጊት ነው ያለው የፓራና ግዛት አቃቤ ህግም በከንቲባው ላይ ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱ ታውቋል።
ማሪለን ሮድ የተባሉት የከንቲባው ሚስት እናት በትምህርት ቢሮ ውስጥ በዝቅተኛ ደመወዝ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር የተባለ ሲሆን፥ በጋብቻ የተሳሰሩት ከንቲባ ያልተገባ ስልጣን ሰጥተዋቸዋል የሚሉ ድምጾች እየተሰሙ ነው።
ከከንቲባው ጋር በ2016 እና 2020 በምርጫ የተፎካከሩትና የከተማዋ የወሳኝ ኩነት ቢሮ ሃላፊ ሂልዳ ሉካልስኪ ሴማ የ65 አመቱን ከንቲባ እና የ16 አመቷን ታዳጊ ጋብቻ ህጋዊ ነው ብለው ማጽደቃቸውም ነው የተገለጸው።
የከንቲባ ሂሳም ሁሴን ዴሃኒ ጽህፈት ቤት በሰጠው ምላሽ “የ26 አመት ልምድ ያላቸውን” (አማታቸውን) ባለሙያ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አድርጎ መሾም ምንድን ነው ነውሩ? ሲል ተከራክሯል።
የፓራና ግዛት አቃቤ ህግ ሹመቱን ከጋብቻው ጋር የተያያዘ ጉቦ ነው ያለው ሲሆን፥ ክስ ለመመስረትም ምርመራ መጀመሩን ነው ያስታወቀው።