የአሜሪካው ኩባንያ ለዩክሬን ሁለት ድሮኖችን በ1 ዶላር ለማቅረብ ማቀዱ አነጋጋሪ ሆኗል
ዋሽንግተንም ሆነች ኬቭ ግን ለጀነራል አቶሚክስ ኩባንያ የሽያጭ እቅድ ምላሽ አልሰጡም
የጦር መሳሪያ አምራቹ ኩባንያ ዝርዝር የሽያጭ እቅድ ሲፈተሽ ግን አነጋጋሪ ሆኗል
የአሜሪካው ኩባንያ ለዩክሬን ሁለት ድሮኖችን በ1 ዶላር ለማቅረብ ማቀዱ አነጋጋሪ ሆኗል።
በአንድ ዶላር ሁለት “ሪፐር ኤምኪው 9” ድሮኖችን ለዩክሬን አቀርባለሁ ያለው የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያ አስገራሚ የሽያጭ እቅድ ይፋ አድርጓል።
ጄነራል አቶሚክስ የተሰኘው ኩባንያ ያቀረበው እቅድ ዝርዝር ሲታይ ግን ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው የሚያስብል ነው።
ኩባንያው ሁለት ድሮኖችን በአንድ ዶላር አቀርባለሁ ቢልም ድሮኖቹን የመስሪያ እና የትራንስፖርት ወጪው ግን የሚቀመስ አይመስልም።
ኬቭ ድሮኖቹን ለመረከብ በጀነራል አቶሚክስ የተጠየቀችው 10 ሚሊየን ዶላር ነው።
በየአመቱም ያረጁ የዩክሬን ድሮኖችን ለመጠገን 8 ሚሊየን ዶላር ሊከፈለኝ ይገባል የሚለው በዝርዝር እቅዱ ውስጥ ተካቷል ይላል የወልስትሪት ጆርናል ዘገባ።
ዩክሬን በየትኛውም አካባቢ የድሮን ጥቃቶችን ለመፈጸም የሚያስፈልጓትን የማዘዣ ጣቢያዎች ለመገንባትም ኩባንያው ፍላጎቱን ገልጿል።
የጀነራል አቶሚክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊንደን ብሉ በዋሽንግተን ለሚገኙት የዩክሬን አታሼ የኩባንያቸውን እቅድ በደብዳቤ ማሳወቃቸውንም ዘገባው ጠቅሷል።
የአሜሪካም ሆነ የዩክሬን መንግስት ግን እስካሁን ስለ1 ዶላሩ የድሮኖች አቅርቦት እቅድ የሰጡት ምላሽ የለም።
ዋሽንግተን ባለፈው አመት ብቻ ከ700 በላይ አነስተኛ ድሮኖችን ለኬቭ ሰጥታለች። እነዚህ ድሮኖች ግን ረጅም ርቀት የማይጓዙና ጥቃቶችን ማድረስ የሚችሉ አይደሉም ነው የተባለው።
ጀነራል አቶሚክስ የሚያመርተው “ሪፐር” የተሰኘው ድሮን ግን በመጠንም ከፍ ያለ እና ረጅም ርቀትን ተጉዞ ኢላማውን መምታት የሚችል መሆኑ ተነግሮለታል።
ከ24 ስአት በላይ መብረር የሚችለው “ራፐር” ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን ወሳኝ ነው ቢባልም የሽያጭ ስምምነቱን የአሜሪካ መንግስት ካላጸደቀው ወደ ኬቭ መግባት አይችልም።
ዋይትሃውስም ራፐር ድሮኖች በጦርነቱ ላይ ቢውሉ በሩሲያ እጅ ሊገቡ ይችላሉ በሚል ወደ ኬቭ እንዲላኩ ይፈቅዳል ተብሎ አይጠበቅም።