በዓለማችን 690 ሚሊየን ሰዎች እራት ሳይበሉ ለመተኛት ይገደዳሉ- የዓለም ምግብ ፕሮግራም
በዓለም ዙሪያ 41 ሚሊየን ሰዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ድርጅቱ አስታውቋል
ለረሃብ አደጋ ለተጋለጡ ሰዎች ለመድረስ በአስቸኳይ 6 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል
በዓለም ዙሪያ 41 ሚሊየን ሰዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
በተለይም በዓለም ዙሪያ በመሰረታዊ የምግብ ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌይ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግማሽ ሚሊየን ገደማ የዓለም ህዝቦች ከረሃብ ጋር ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
“በአሁኑ ሰዓት በ4 ሀገራት ከረሃብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክስተት ተፈጥሯል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “41 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ደግሞ የረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ ቆመዋል” ብለዋል።
ለረሃብ አደጋ የተጋለጡት 41 ሚሊየን ሰዎች በ43 ሀገራት ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ለእነዚህ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
“የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገናል እሱንም አሁን በአፋጣኝ ነው ሊደርሰን የሚገባው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ ዴቪድ ባስሌይ።
ለበርካታ ዓመታት የመቀነስ አዝማሚያ ተስተውሎበት የነበረው በዓለም ለረሃብ አደጋ የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከፈረንጆቹ 2016 ዓመት ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭቶች ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአውሮፓውያኑ በ2019 በዓለም ዙሪያ ለረሃብ አደጋ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር 27 ሚሊየን የነበረ ሲሆን፤ በ2020 የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ተጽእኖ ተከትሎ ቁጥሩ በፍጥነት አሻቅቧል።
ባሳለፍነው ግንቦት ወር በዓለም ላይ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
እንደ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቬንዙዌላ እና ሊባኖስ ያሉ ሀገራት ከዶላር አንጻር ገንዘጋባቸውን መግዛት አቅም ዝቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ በሀገራቱ የምግብ አቅርቦት ዋስትናን አደጋ ላይ መጣሉም ተመላክቷል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው ከሆነ በዓለም ላይ ካለ የህዝብ ቁጥር ውስጥ 9 በመቶ ማለትም 690 ሚሊየን ሰዎች በእያንዳንዱ ምሽት ምግብ ሳይበሉ ወደ መኝታቸው ያቀናሉ።