“የዓለም የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት ጭማሪ እያሳየ ነው” - ተመድ
የምግብ ፈላጊው ቁጥር ከፍተኛ መሆን እና የምርት ማነስ የዋጋ ንረቱን ይበልጥ እንዳያባብስ ተሰግቷል
በግንቦት ወር ብቻ የዓለም የምግብ ዋጋ በ39 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
የዓለም የምግብ ዋጋ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ላለፉት አስር ዓመታት ባልታየ መልኩ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ጠቋሚ መረጃን መሰረት በማድረግ እንዳስታወቀው የዓለም የምግብ ዋጋ በተከታታይ ለ12 ወራት ጭማሪ አሳይቷል።
የተመድ የምግብና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) በዓለም ዙሪያ ስጋ፣ ስኳር እና የቅባት እህሎችን ጨምሮ የሌሎች ምግቦችን ዋጋ ክትትል ሲያደርግ ነበር።
በዚህም በግንቦት ወር ብቻ የዓለም የምግብ ዋጋ በ39 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በአውሮፓውያኑ ከ2010 ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
አትክልትና ፍራፍሬ፣ እህል እና ስኳር ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለታየው የምግብ ዋጋ ንረት ዋነኛው መንስኤ መሆኑም ነው የተመላከተው።
በሀገራት ያለው የፍላጎት መጨመር፣ የምርት ማነስ እና ሀገራት ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዳይቀርቡ መከልከላቸው የምግብ ዋጋ ጭማሪውን ማስከተሉንም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።
የምግብ ፈላጊዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን እና የምርት ማነስ ፣ የበርካታ ሀገራት የኢኮኖሚ እንቅቃሴ ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቀመጠው ገደብ በሚነሳበት ጊዜ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል ሲሉም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሳስበዋል።