በሶማሊያ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ከ60ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተመድ ገለጸ
በግጭቱ ምክንያት ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ከ185 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን ወደ ተለያዩ ሀገራት ተሰዷል
ተመድ፤ “በየቀኑ በአማካይ 1000 ሶማሊያውያን ወደ ኢትዮጵያ ይሻገራሉ” ብሏል
በቅርቡ በሶማሊያ ሱል ክልል በላሶን ከተማ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ከ60ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ኢትዮጵያ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታታ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ግጭቱን በመሸሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡት አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት ሲሆኑ፤ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው ተብሏል፡፡
ኬንያ ከ10 አመታት በኋላ ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስናትን የማንዴራ ድንበር ልትከፍት ነው
ሰዎቹ በከፍተኛ ድካምና ጭንቀት ህይወታቸውን ማትረፍ የቻሉት ሲሆን ኢትዮጵያ ለመድረስ ያላቸውን ንብረት ሁሉ እንደሸጡም ነው ከሸሹት እንዷ የሆነችው ሴት ለተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የተናገረችው፡፡
ብዙዎቹ በግጭቱ ምክንያት ዘመዶቻቸውን ያጡ ወይም በበረራ ወቅት የተለያዩ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሶማሊያውያኑ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በዶሎ ዞን በቡክ፣ ጋልሀሙር እና በዳኖት ወረዳሺን ከተሞች ከ13 በላይ በሆኑ ቦታዎች በጊዜያዊነት እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡
የአከባቢው ማህበረሰብ አስከፊ ድርቅ ባለበት አከባቢ የሚገኝ ቢሆንም ያለውን በማካፈል ስደተኞቹን በልግስና መቀበሉንም ነው ድርጅቱ የገለጸው፡፡
“በየቀኑ በአማካይ 1000 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ይሻገራሉ” ያለው የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ፤ እየጨመረ ካለው ቁጥር አንጻር አስፈላጊውን ድጋፍ ሊደረግ ይገባልም ብሏል፡፡
“የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ፣ የውሃ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲሁም የተለየ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ልዩ ድጋፍ ይሻሉ”ም ነው ያለው ኤጀንሲው፡፡
የተባበሩት መንግታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በድንገት ለተከሰተው ፍልሰት ምላሽ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ፣ ከሶማሌ ክልል ባለስልጣናት እንዲሁም ከተመድ አጋሮእ እና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን ጊዜያዊ መቀበያ ማዕከላትን በማቋቋም እና አፋጣኝ የህይወት አድን እርዳታዎችን በማቅረብ ላይ እንሚገኝም ገልጿል።
እስካሁን ከ1000 በላይ ለሆኑ ተጋላጭ ቤተሰቦች ብርድ ልብሶች፣ ጀሪካኖች፣ ባልዲዎች፣ የወጥ ቤት እቃዎች፣ የፕላስቲክ አንሶላዎች እና የወባ ትንኝ አጎበርን ጨምሮ የእርዳታ እቃዎች ማከፋፈሉም አስተውቋል ዩኤንኤችሲአር፡፡
በሚቀጥሉት ቀናት ሌሎች 9000 ቤተሰቦችን የመድረስ አላማ እንዳለው የገለጸው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአከባቢው የጸጥታ ሁኔታ እየተሸሻለ ሲሄድ ለ3 ወራት ያህል ለ42ሺህ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝም ጭምር አስታውቋል፡፡
በሶማሊያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ከ185 ሺህ በላይ ሰዎች ከላስካኖድ ከተማ እና አካባቢዋ ወደ የተለያዩ ሀገራት ድንበር አቋርጠው መሰደዳቸው የተመድ መረጃ ያመለክታል።
በአካባቢው ባለስልጣናት እንደተናገሩት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች በሶማሌላንድ ውስጥ በ66 ቦታዎች ሲሰፍሩ ሌሎች ደግሞ ወደ ፑንትላንድ እና ሰሜናዊ ሶማሊያ ተሰደዋል እንዲሁም የኢትዮጵያ አዋሳኝ መንደሮች ገብተዋል።