ሶማሊያ ከ32 ዓመት በኋላ ኢምባሲዋን በብሪታንያ ከፈተች
በለንደን በተከፈተው የሶማሊያ ኢምባሲ ፕሮግራም ላይ ትውልደ ሶማሊያውያን ዲያስፖራዎች ተገኝተዋል
ሶማሊያ ባጋጠማት የመንግስት መፍረስ ምክንያት በለንደን የነበራትን ኤምባሲ ለመዝጋት ተገዳ ነበር
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከ32 ዓመት በኋላ በለንደን ኢምባሲዋን ከፍታለች።
ሶማሊያ ከዚህ በፊት በብሪታንያ ኢምባሲ የነበራት ቢሆንም ባጋጠማት የመንግስት መፍረስ ምክንያት ለመዝጋት ተገዳለች።
አልሻባብ እስላማዊ መንግሥት በሀይል ለመመስረት በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበረው መንግሥት ላይ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ከመፍረሱ በተጨማሪ በብዙ ሀገራት የነበሯትን ኢምባሲዎች ዘግታ ቆይታለች።
በትናንትናው ዕለትም ሶማሊያ በለንደን የነበራትን ኢምባሲ ዳግም የከፈተች ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ በዜግነት እንግሊዛዊ በትውልዱ ደግሞ ሶማሊያዊው አትሌት መሀመድ ፋራህ እና ሌሎችም መገኘታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በለንደን የተከፈተው የሶማሊያ ኢምባሲ ለ500 ሺህ ዲያስፖራ ሶማሊያውያን አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ከአልሻባብ ጋር ብርቱ ጦርነት እያደረገ ያለው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ አልሻባብን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ማቀዷን ገልጻለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራት የሶማሊያ ጦርን ለማሰልጠን የተስማሙ ሲሆን ሶማሊያ እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስም 30 ሺህ ጦር እንደምታሰለጥን ከዚህ በፊት መናገሯ አይዘነጋም።
ብሪታንያ በፈረንጆቹ 2013 ላይ ከ22 ዓመት በኋላ ዳግም ኢምባሲዋን በሞቃዲሾ መክፈቷ ይታወሳል።