የተገደለው አመራር የአይኤስ እንቅስቃሴ በአፍሪካ እንዲስፋፋ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረ ነው ተብሏል
የአሜሪካ ጦር በሰሜን ሶማሊያ ባካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ የአይኤስ ከፍተኛ አመራር ነው የተባለውን ግለሰብን ጨምሮ 11 የሽብር ቡድኑ አባላትን መግደሉን አስታወቀ፡፡
የተገደለው አመራር ቢላል አል-ሱዳኒ በመባል የሚታወቅና ማዕከሉን "በሰሜን ሶማሊያ ከሚገኝ ተራራማ ዋሻ” በማድረግ የአይኤስ እንቅስቃሴ በአፍሪካ እንዲስፋፋ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረ መሆኑም ነው ኒውዮርክ ታይምስ የፔንታጎን መረጃን ጠቅሶ የዘገበው፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በሰጡት መግለጫም በአፍሪካ የአይኤስ ክንፍ የሚመራው አል-ሱዳኒ መገደሉን አረጋግጠዋል።
"በፕሬዝዳንት ባይደን ትእዛዝ መሰረት የአሜሪካ ጦር ጥር 25 በሰሜናዊ ሶማሊያ ባካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በሶማሊያ የአይኤስ መሪና የቡድኑ ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ ዋና አመቻች የሆነውን ቢላል አል-ሱዳኒን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላት ተገድለዋል፡፡
አል-ሱዳኒ በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የአይኤስ ይዞታ ለማስፋፋት እንዲሁም አፍጋኒስታንን ጨምሮ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚያደረገው እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት የነበረው ነው” ሲሉም ተናግረዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ፡፡
በዘመቻው በሲቪሎች ላይ የደረሰ አንዳችም ጉዳት የለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዘመቻው አል-ሱዳኒን ለመያዝ በማቀድ የተካሄደ ቢሆንም ከነበረው አስችጋሪ ሁኔታ (የቡድኑ አባላት የተኩስ ምላሽ) አንጻር እርምጃ ተወስዶበት ሊገደል ችሏል ብለዋል፡፡
አሜሪካ ከአልሻባብ ውጭ በሆነው ኃይል (አይኤስ) ላይ በሶማሊያ ምድር ወታደራዊ ዘመቻ ስታካሂድ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ጦር ባለፈው አመት መጨረሻ አካባቢ በሶሪያ ባደረገው የአየር ድብደባ ሁለት ከፍተኛ የአይኤስ መሪዎችን መግደሉ አይዘነጋም፡፡
ዘመቻው ከ20 ዓመታት በኋላ ጦራቸውን ከአፍጋኒስታን ያወጡት ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ባደረጉት ስትራቴጂያዊ ለውጥ ትኩረታቸውን “ሽብርተኝነትን መከላከል” ላይ ማድረጋቸውን የሚያመላክት እንደሆነ ይገለጻል፡፡
በአሁኑ ዘመቻ የተገደለው አል-ሱዳኒ እንደፈረንጆቹ በ2012 የውጭ ተዋጊዎች ወደ አልሸባብ ማሰልጠኛ ካምፕ እንዲጓዙ በመርዳት እና የገንዘብ ድጋፍን በማመቻቸት በሚል በአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀብ ተጥሎበት የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡