ኬንያ ከ10 አመታት በኋላ ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስናትን የማንዴራ ድንበር ልትከፍት ነው
ኬንያ እና ሶማሊያ በድንበር የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር በጋራ ለመስረት ከስምምነት ደርሰዋል
ኬንያ፤ የአልሸባብን ወረራ ለማስቆም በሚል የማንዴራን ድንበር የዘጋችው እንደፈርንጆቹ በ2012 ነበር
ኬንያ ከ10 አመታት በኋላ ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስናትን የማንዴራ ድንበር ልትከፍት ነው፡፡ ኬንያ ድንበሩን ክፍት የምታደርገው ሁለቱን ሀገራት የድንበር ደህንነትን ለማሻሻል እና የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር በጋራ ለመስራት ምክክር ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
በማንዴራ ከተማ ጉብኝት ያደረጉት የኬንያ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ኪቱሬ ኪንዲኪ ፤ የድንበሩ እንደገና መከፈት በአከባቢው ያለውን ደህንነትን ከማሻሻል በዘለለ ለሽብር ተግባራት የሚውሉ የኮንትሮባንድ እቃዎች ለመቆጣጠር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
"ድንበራችንን እንደገና ለመጀመር የግዛቱን የጸጥታ ኃይል ከጉምሩክን እና ኢሚግሬሽን በተጨማሪ እዚህ ከሚወከሉት የመንግስት ኤጀንሲዎች ጋር እንዲመክርና ያለውን ሁኔታ በመገምገም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መረጃ እንዲሰጡን አዝዣለሁ”ሲሉም ነው የተናገሩት ክንዲኪ።
ኬንያ በሶማሊያ በኩል የሚንቀሳቀሱትን የአልሸባብ ታጣቂዎች ወረራ ለማስቆም በሚል እንደፈረንጆቹ በ2012 ከሶማሊያ ጋር ያሏትን ይፋዊ የድንበር ማቋረጫዎችን በሙሉ መዝጋቷ የሚታወስ ነው።
እንደ ማንዴራ ሁሉ በላሙ፣ ዋጂር እና ጋሪሳ የሚገኙ የድንበር ማቋረጫዎች ተዘግተው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ኬንያ ድንበሮችን ብትዘጋም ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር እንዳይሻገሩ እና እቃዎችን ከማዘዋወር ያገዳቸው ነገር አልነበረም፡፡
ኪንዲኪ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱትን የአልሸባብ ታጣቂዎችን የመለየት ስራ ለግዛቱ የጸጥታ ኃይል ኃላፊነት እንደተሰጠም አስታውቀዋል፡፡
የጸጥታ ኃይሉ ከፖለቲካ መሪዎች፣ ከህብረተሰቡና እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር በማንዴራ እና በሰሜን ምስራቅ አከባቢዎች የሚገኙ ታጣቂዎችን የማስቀገድ ተልእኮ የሚወጣ ይሆናም ብለዋል፡፡
የኬንያ ሰሜናዊ ምስራቅ ላለፉት አምስት አመታት በአልሸባብ ታጣቂዎች ተከታታይ ጥቃቶች ሲሰነዘርበት የቆየ አከባቢ ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2015 አልሸባብ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፈጸመውና 150 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉበት አሳዛኝና አስከፊ ጥቃት የማይረሳ ነው፡፡
ዋና ይዞታው ሶማሊያ ያደረገው አልሸባብ እንደፈረንጆቹ ከ2011 ወዲህ የቀጠናው ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኬንያ ጸረ-አልሸባብ በሚደረገው ዘመቻ በሶማሊያ ለሚገኘው በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ስር ወታደሮቿን ያሰማራች ሀገር መሆኗም ይታወቃል፡፡