78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ነገ በኒውዮርክ ይጀመራል
የ150 ሀገራት መሪዎች በሚሳተፉበት ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ እና የዩክሬን ጦርነት ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል
በጉባኤው ዩክሬን በፕሬዝዳንቷ ሩሲያ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ይወከላሉ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ነገ በኒውዮርክ ይጀመራል።
በ78ኛው ጉባኤ የ150 ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ለአለም ሀገራት የጋራ መጻኢ ይመከርበታል ብለዋል የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።
የአለም መሪዎች በቀጣዩ አመት በሚያተኩሩባቸው የጋራ ጉዳዮች እና አንገብጋቢ ጉዳዮች የሚመክሩበት ጉባኤ የተመድ ትልቁ አመታዊ ስብሰባ ነው።
በ78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ አለምን እየፈተነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ እና የዩክሬን ጦርነት ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ይሆናሉ ተብሏል።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በጉባኤው የመጀመሪያውን ንግግር ሲያደርጉ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሀገራቸው እየሰራች ያለውን ስራ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ሉላ ዳ ሲልቫን ተከትለው ንግግር እንደሚያደርጉ ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም በጉባኤው ንግግር እንደሚያደርጉና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ከጉባኤው ጎን ለጎን እንደሚመክሩ ተዘግቧል።
በመንግስታቱ ድርጅት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ካላቸው አምስት ሀገራት ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ በ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በመሪዎቻቸው አይወከሉም።
በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሰርጌ ላቭሮቭ ወደ ኒውዮርክ እንደሚልኩ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የብሪታንያ እና ፈረንሳይ መሪዎች ግን በሌላ ስራ መጠመዳቸውን በመግለጽ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ነው የገለጹት።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግም ነገ በሚጀምረው ጉባኤ ይሳተፋሉ ተብሎ አይጠበቅም።
በዚህ ጉባኤ ሀገራት በዩክሬን ላይ ጦርነት በከፈተችው ሩሲያ ላይ ጫናቸውን እንዲያበረቱ ምክክር ይደረጋል።
በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ የተደረጉ የመንግስት ግልበጣዎች፣ የሱዳን እና ኢትዮጵያ ግጭቶችም የጉባኤው አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሏል።