ተመድ በዩክሬን የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን 'አደጋ የተደቀነባቸው' ቦታዎች ዝርዝሩ ላይ አሰፈረ
ዩኔስኮ በጦርነቱ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጠበቅ የተቀመጡ ሁኔታዎች አልተከበሩም ብሏል
ሩሲያ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እንደምታደርግ ቃል ገብታለች
በዩክሬይን ሁለት ግዙፍ ታሪካዊ ከተሞች በጦርነቱ ምክንያት አደጋ ላይ ናቸው ተብሏል።
የዓለም የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) እንዳስታወቀው በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዋና ከተማዋ ኪየቭና ሌቪቭ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
በዝርዝሩ በኪየቭ የሚገኙ ታዋቂው የቅድስት ሶፊያ ካቴድራልና የላቭራ ገዳም የመካከለኛ ዘመን ህንጻ ይገኙበታል።
የሌቪቭ የከተማው ታሪካዊ መሀል ክፍል በዩኔስኮ አደጋ የተደቀነባቸው ታሪካዊ ስፍራዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።
ዩኔስኮ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጠበቅ የተቀመጡ ሁኔታዎች አልተከበሩም ብሏል።
"እነዚህ ታሪካዊ ስፍራዎች ለቀጥታ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው። በሁለቱ ከተሞች አስደንጋጭ የቦንብ ድብደባ ስጋት ጥሎባቸዋል" በማለት ገልጿል።
ድርጅቱ ከተሞችን በአደገኛ ስጋት ዝርዝሩ ያካተታቸው የመንግስታቱ ድርጅት አባላት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው ብሏል።
እርምጃው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎችን ለማግኘትም ይጠቅማል ሲል አክሏል።
ሩሲያ ለተመድ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እንደምታደርግ ቃል ገብታለች። ሆኖም ዩክሬን ቃሉ እንዳልተከበረ በተደጋጋሚ ተናግራለች።