ተመድ የሱዳን ጦርነት የሀገሪቱ እጣፈንታ እና መላውን ቀጣናውን አለመረጋጋት ላይ ሊጥል ስለሚችል አሳስቦኛል አለ
በግጭት የምትታመሰው ሱዳን አጠቃላይ ቀጣናውን አለመረጋጋት ላይ ሊጥል የሚችል "የእርስ በርስ ጦርነት" አፋፍ ላይ መሆኗን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
ተመድ ማስጠንቀቂያውን ያወጣው በአንድ የመኖሪያ ሰፈር ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ሁለት ደርዘን የሚጠጉ ንጹሀን ዜጎችን ከገደለ በኋላ ነው።
ቅዳሜ ዕለት በካርቱም እህት ከተማ ኦምዱርማን በዳር አል-ሰላም የአየር ጥቃት 22 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታውቋል።
በሱዳን ተቀናቃኝ ጄኔራሎች መካከል የፈነዳውና ሦስት ወራትን በተጠጋው ጦርነት የአየር ድብደባው ቁጣን ቀስቅሷል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
በግጭቱ ወደ ሦስት ሽህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል የተባለ ሲሆን፤ ከአደጋ በተረፉ ሰዎች ደግሞ የጾታዊ ጥቃት ማዕበል ከፍ እንዳለ ተነግሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዳርፉር ክልል በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን አስጠንቅቋል።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኦምዱርማን የተካሄደውን የአየር ጥቃት አውግዘዋል፤ "የቀጠለው ጦርነት ሱዳንን ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ እየገፋት እና መላውን ቀጣናውን አለመረጋጋት ላይ ሊጥል ስለሚችል በጣም ያሳስበናል" ማለታቸውን ቃል አቀባያቸው ገልጸዋል።