ከሰው ልጅ ተነጥቀው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚተኩ የስራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
የአሜሪካው ቻትጅፒቲ በሰው ልጆች ተይዘው የነበሩ ብዙ ስራዎችን ሊተካ ይችላል ተብሏል
በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሊያዙ ይችላሉ የተባሉ የዓለማችን ስራዎች ይፋ ሆነዋል
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚተኩ የስራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
በየጊዜው ይፋ የሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሰው ልጆችን ህይወት በማቅለል ይታወቃሉ።
እነዚህ ፈጠራዎች በየጊዜው እየዘመኑ እና እየተሻሻሉ የመጡ ሲሆን አንዳንዶቹ መልሰው የሰው ልጆችን ፍላጎት ሲጋፉ ይስተዋላል።
በቀርቡ በአሜሪካው ኦፕን አይ ኩባንያ ይፋ የተደረገው ቻትጅፒቲ የቴክኖሎጂ ስራ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ብዙዎችን አስገርሟል።
የሙዚቃ ግጥም እና ዜማን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን ይሰራል የተባለው ቻትጅፒቲ አሁን ደግሞ በሰው ልጆች ይሰራሉ የተባሉ እልፍ ስራዎችን በመረከብ በፍጥነት ያከናውናል ተብሏል።
የሰው ልጅ ህዝብ ቁጥር እና የስራ ፍላጎት እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ ቴክኖሎጂ ሰዎችን ተክቶ መስራቱ ጉዳቱ ያመዝናልም እየተባለ ይገኛል።
ዩሮ ኒውስ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ይዞት በወጣው ዘገባ መሰረት በቻትጅፒቲ ቴክኖሎጂ ሊተኩ የሚችሉ ስራዎችን እንደሚከተለው አስቀምጧል።
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት በቻትጅፒቲ ቴክኖሎጂ ብዙ ስራዎች በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ሊተኩ ይችላሉ ብለዋል።
ከቋንቋ ጋር የተያያዙ 86 የስራ ዘርፎች ሙሉ ለሙሉ በቻትጅፒቲ ሊተኩ ይችላሉ የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ 15 ጠቅላላ የሙያ መስኮች በዚሁ ቴክኖሎጂ ይተካሉ ተብሏል።
ከዚህ በፊት በሰው ልጆች ሲከናወኑ የነበሩ በቀጣይ ግን ሙሉ ለሙሉ በቻትጅፒቲ ቴክኖሎጂ ይተካሉ ከተባሉ ሙያዎች ውስጥም የሒሳብ ስራ፣ የግብር መረጃ ዝግጅት ፣ የፋይናንስ ትንታኔዎች፣ ድርሰት እና ጽሁፍ ስራዎች፣ የዌብሳይት ዲዛይን እና ማስተዳድር ስራዎች ዋነኛዎቹ ናቸው።
እንዲሁም የጥናት ስራዎች፣ትርጉም ስራዎች፣ የህዝብ ግንኙነት ፣ የእንስሳት ሳይንስ እና ከቋንቋ ጋር የተያያዙ ሌሎች ስራዎችም ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል በዚህ ቴክኖሎጂ ሊከናወኑ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም የጋዜጠኝነት ስራዎች፣ የአየር ንብረት ፖሊሲ፣ ክሊኒካል ዳታ ፣ የህግ ጉዳዮች ጽህፈት፣ የፍርድ ቤት ሪፖርት እና የአርትኦት ስራዎች በቻትጅፒቲ ሊከናወኑ እንደሚችሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ይሁንና ይህ የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ የተሳሳቱ ውጤቶችን እና ሪፖርቶችን የመስራት እድሉ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።