“ሜሲን የምትበልጠው” ሮቦት ተጫዋች
“አርትሚስ” የተሰኘችው ሮቦት በአለማችን በፍጥነት ከሚሮጡና ኳስን በብቃት ከሚያንቀረቅቡ ሶስት ሮቦቶች አንዷ ናት ተብሏል
ፈረንሳይ ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሳተፉበትን የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድርን በዚህ አመት ታስተናግዳለች
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መሮጥና መዝለል ትችላለች ያላትን እግርኳስ ተጫዋች ሮቦት አስተዋውቋል።
1 ሜትር ከ46 ሴንቲሜትር የምትረዝመው ሮቦት በአለማችን በፍጥነት ከሚሮጡና ከሚዘሉ ሮቦቶች ሶስተኛዋ ናት ተብሏል።
“አርትሚስ” የሚል ስም የተሰጣትን ተጫዋች የሰሩት ተመራማሪዎች ሮቦቷ “ሜሲን ትበልጣለች” ሲሉ ቀልደዋል።
በሰከንድ 2 ነጥብ 1 ሜትር የምታካልለው “አርትሚስ” የእግር ኳስ ክህሎት በሀምሌ ወር 2023 በፈረንሳይ በሚደረገው የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር ይታየል ነው የተባለው።
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሮቦቲክስ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተሩ ዴኒስ ሆንግ፥ የእግር ኳስ ተጫዋቿ ሮቦት መበልጸግ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ለአለም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እየሮጠችና ኳስ እያንቀረቀበች ልምምድ የሰራችው “አርትሚስ” ከሜሲ በተወሰነ መልኩ የተዋሰችውን ስም የሚመጥን ብቃት እንደምታሳይም ተስፋ አድርገዋል።
በፈረንሳይ በሚደረገው የ2023 የሮቦቶች ዋንጫ ከ45 ሀገራት የተወከሉ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሮቦቶች እንደሚሳተፉ ነው የተነገረው።
ከ30 አመት በፊት የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር እንዲካሄድ ሃሳብ ያቀረበው ሂሮኪ ኪታኖ፥ ሮቦቶች በ2050 ከሰው ልጆች ጋር በእግር ኳስ ሜዳ ተሰልፈው መጫወት እንደሚችሉ ያምናል።
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የበለጸገችው “አርትሚስ”ም በቀጣይ ሳምንታት የሜዳ ላይ ልምምዷን ትቀጥላለች የተባለ ሲሆን፥ የወደቁ እቃዎችን ጎንበስ ብላ ማንሳትን ጨምሮ የተለያዩ አዳዲስ ልምምዶችን እንደምታደርግ ተገልጿል።
38 ኪሎግራም የምትመዝነው እግርኳስ ተጫዋቿ ሮቦት የሰውነት ክፍሎቿ እንዳሻቸው እንዲተጣጠፉ ተደርገው መሰራታቸው ዳገትም ሆነ ቁልቁለት ለመጓዝና ለመሮጥ ያስችላታል ነው የተባለው።
“አርትሚስ”ን የሰራው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደምም “ሳፊር” የተሰኘ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ሮቦትን በፈረንጆቹ 2014 መስራቱን ዴይሊ ሜል በዘገባው አስታውሷል።