የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በከፍተኛ ደመወዝ ያወጡት የስራ እድሎች የትኞቹ ናቸው?
አማዞን እና ጎግል በከፍተኛ ደመወዝ ክፍት የስራ እድል በማዘጋጀት ቀዳሚ ሆነዋል
ኩባንያዎቹ ከ130 ሺህ እስከ 230 ሺህ ዶላር ደመወዝ እንደሚከፍሉም ተመላክቷል
ዓለም አቀፍ ከፍት የስራ ቦታዎችን የሚያወጣው Comprehensive.io ድረ-ገጽ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያላቸውን የስራ እድሎች እና ደመወዝ በአሃዝ አስደግፎ ይፋ አድረጓል።
ቢዝነሰ እንሳይደር በድረ ገጹ ያወጣው የComprehensive.io ድረ-ገጽ መረጃ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድሎች ሰዎች ጥሩ ስራን እና ጥሩ ክፍያን እንዲያማርጡ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የስራ እድል መረጃው በዓለም ዙሪያ ካሉ 700 የቴክኖሎጂ ኩባያዎች የተሰበሰበ ነው የተባለ ሲሆን፤ ከኩባንያዎቹ መካከልም ከፍተኛ ከፋይ የሆኑት ጎግል እና አማዞን ይገኙበታል።
በኩባንያዎቹ ያሉ የስራ እድሎችና ከፍያቸው
የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ዳይሬክተር፤ በዚህ መስክ በ80 ኩባንያዎች ውስጥ 405 ክፍት የሥራ ቦታዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ ክፍያቸውም በዓመት በአማካይ ከ174 ሺህ እስከ 210 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው።
ሶፍትዌረ ኢንጂነር፤ በዚህ መስክም በ53 ኩባንያዎች ውስጥ 285 ክፍት የሥራ ቦታዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ ኩባንያዎቹ በዓመት በአማካይ ከ132 ሺህ እስከ 200 ሺህ የዓሜሪካ ዶላር ደመወዝ እንደሚከፍሉም ተመላቷል።
የፕሮዳክት ማናጅመንት ዳይሬክተር፤ በዚህ መስክ 151 የስራ እድሎች በ51 ኩባንያዎች ውስጥ ወጥቷል የተባለ ሲሆን፤ ዓመታዊ ደመዛቸውም በአማካይ ከ152 ሺህ እስከ 208 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው ተብሏል።
የኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር፤ በዚህ የስራ መስክ በ36 ኩባንያዎች ውስጥ 83 ክፍት የሥራ ቦታዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ ዓመታዊ አማካይ ደመወዛቸውም ከ173 ሺህ እስከ 234 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው መሆኑም ተጠቅሷል።
ዳይሬክተር ኦፍ ቴክኒካል ሰፖርት፤ በዚህ የስራ መስክ በ14 ኩባንያዎች ውስጥ 43 ክፍት የሥራ ቦታዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ ዓመታዊ አማካይ ደመወዛቸውም ከ147 ሺህ እስከ 201 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው።
ዝርዝር ክፍት የስራ ሁኔታዎቹን እና የክፍያመረጃውን Comprehensive.io ድረ-ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል።