ጎግል የስራ ማመልከቻን ጨምሮ ስራን የሚያቀል ሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዋወቀ
አዲሱ አገልግሎት የኢሜል መልዕክቶችን ከመጻፍ ባሻገር ለተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው ተብሏል
የአልፋቤት እህት ኩባንያ የሆነው ጎግል ከቻትጂፒቲ የገጠመውን ብርቱ ፉክክር ተከትሎ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ነው
ጎግል ለደንበኞቹ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ይፋ አድርጓል።
በጎግል ወርክስፔስ እና ጂሜል ላይ የሚቀርበው አገልግሎት በአሜሪካ በተወሰኑ ሰዎች እንዲሞከር ተደርጓል።
አዲሱ ሲስተም የጂሜል መልዕክቶችን፣ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ ስላይዶችን ማዘጋጅት ይችላል የተባለ ሲሆን፥ በስብሰባዎች ላይ የተያዙ አጫጭር ማስታወሻዎችን ዘርዘር አድርጎ ማቅረብም እንደሚችል ተነግሮለታል።
ተጠቃሚዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረትም የጽሁፍ፣ የምስል እና ቪዲዮ ቅንብሮችን ሰርቶ እንደሚያቀርብ ነው የአልፋቤት እህት ኩባንያ የሆነው ጎግል ያስታወቀው።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንሱ “የሽያጭ ሰራተኛ የስራ ማመልከቻ (ሲቪ) እንዲጽፍ ተጠይቆ የተሟላና በተጠቃሚው የተወሰነ ማስተካከያ ሊደረግበት የሚችል ማመልከቻ በሰከንዶች ውስጥ መስጠቱ በሬውተርስ ዘገባ ላይ ሰፍሯል።
ጎግል በሰው ሰራሽ አስተውሎት ከቻትጂፒቲ እና ማይክሮሶፍት ብርቱ ፉክክር እንደገጠመው ተነግሯል።
ቻትጂፒቲ በዛሬው እለት ጽሁፍን ወደ ቪዲዮ ምስል ቀይሮ የሚያቀርብ “ቻትጂፒቲ 4” የተሰኘ ቻትቦት ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ጎግልም ከዚህ የቻትጂፒቲ አዲስ አገልግሎት በፊት በሙከራ ደረጃ ያስተዋወቀው ቻትቦት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የገቡበትን ፉክክር በጉልህ አሳይቷል።
አዲሱ አገልግሎቱ በተለይ የወርክስፔስ ተጠቃሚዎችን ጊዜና ጉልበት በእጅጉ የሚቆጥብና ለማንኛውም ጥያቄ ፈጣንና ታማኝ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ጎግል አስታውቋል።
ጎግል ክላውድም በተለያዩ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በጽሁፍ፣ ፎቶ እና ቪዲዮ የሚመልስ ቻትቦት ይኖረዋል ነው የተባለው።
የጎግል እናት ኩባንያ አልፋቤትም ሆነ የቻትጂፒቲው ኦፕን ኤ አይ እና ማይክሮሶፍት ቢሊየን ዶላሮችን በመመደብ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ በስፋት እየሰሩ ነው።