የ90ኛ አመት ልደታቸውን በአፍሪካ ሁለተኛውን ረጅም ተራራ በመውጣት ያከበሩት አሜሪካዊ
ትውልደ ኤርትራዊው አዛውንት ማውንት ኬንያን 14 ጊዜ መውጣታቸው ተነግሯል
አሜሪካዊው አዛውንት ሰዎች የሚያስደስታቸውን ነገር ለማድረግ ፍርሀት እንዳይገድባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል
አሜሪካዊው ናይዝጊ ገብረመድህን በ90 አመታቸው በአፍሪካ በርዝመቱ ሁለተኛ የሆነውን ማውንት ኬንያን መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡
ትውልደ ኤርትራዊው ናይዝጊ 5199 ሜትር የሚረዝመውን የኬንያ ተራራ ደጋግመው በመውጣት ጥንካሬያቸውን አሳይተዋል።
በቅርቡም የ90 አመት ልደታቸውን ሲያከብሩ ተራራውን የወጡ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ተራራውን 14 ጊዜ መውጣታቸውም ተዘግቧል።
ተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ ከ6-7 ሰአታት የፈጀባቸው ሲሆን ተራራውን ከመውጣት ይልቅ መውረዱ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ተራራ የመውጣት ልማድ ያላቸውአዛውንቱ 5895 ሜትር የሚረዝመውን በአፍሪካ ትልቁን ኪሊማንጃሮ ተራራን መውጣት ችለው ነበር፡፡
ናይዝጊ የ90 አመት ልደቴን ለማክበር ከዚህ የተሸለ ቦታ የለም ሲሉ ተራራውን ወጥተው ከጨረሱ በኋላ ተናግረዋል፡፡
አክለውም በእኔ እድሜ ለሚገኙ ሰዎች ነገሩ ቀላል ላይሆን ትንሽ ግራ ሊያጋባም ይችላል ነገር ግን ህይወት አጭር ናት ሰዎች የሚያስደስታቸውን ነገር ለማድረግ ፍርሀት ሊይዛቸው አይገባም ነው ያሉት፡፡
እርጅና ባልመጣ የሚያስበላው ሰዎች በአንድ ቦታ ብቻ ተወስነው ለማሳለፍ ሲወስኑበት ነው ያሉት አዛውንቱ አዳዲስ ነገሮችን ለማየት እና ለመሞከር እንደ እርጅና አመቺ ጊዜ የለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሰዎች በእርጅና ዘመን ሁሉም ነገር እንዳበቀ ተቀብለው ከመኖር ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ቢያዘወትሩ እና አመጋገባቸውን ማስተካከል ቢችሉ ከእድሜ ጋር የሚመጡ ጫናዎችን መቋቋም እንደሚቻልም ነው የሚናገሩት፡፡
በተጨማሪም በቀን 10ሺህ እርምጃዎችን መራመድ ፣ ፑሽአፕ እና የሰውነት ማሳሳብን መሰል ስፖርታዊ እንቅስቃሴውችን ያለምንም ችግር እንደሚያከናውኑ ሰውነታቸው በእርጅና እንዳይደክም ስፖርት እንዳገዛቸው ያነሳሉ፡፡
የአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ፋካሊቲ ዲን ሆነው እንዳገለገሉ የሚናገሩት ናይዛጊ የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ በዩኒስኮ እንድትመዘገብ ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ ቪኦኤ ዘግቧል፡፡